Top

20

ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በሳምንቱ መጨረሻ በተደረጉ የተለያዩ የማራቶን ውድድሮች ድል ቀንቷቸዋል

Monday 18th of April 2016 08:51:03 AM  |  Ethio Tube

መሰለች መልካሙ እና ተስፋዬ አበራ የሀምቡርግ፣ ሻሾ ኢንሰርሙ የናጋኖ፣ አብራራው ምስጋናው የዶዝ ሎድዥ ማራቶን ውድድሮች አሸንፈዋል

Tesfaye-Abera.jpg

Meselech-Melkamu.jpg

የ2016 ሀምቡርግ ማራቶን አሸናፊዎቹ መሰለች መልካሙ እና ተስፋዬ አበራ (ከላይ) ውድድሩን በድል ሲያጠናቅቁ (Photo © Hochzwei)

በሳምንቱ መጨረሻ (ሚያዝያ 9 ቀን 2008 ዓ.ም.) በተለያዩ ሀገራት በተደረጉ የማራቶን ውድድሮች ላይ ተሳታፊ ከነበሩት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች መካከል ሁለት ወንድ እና ሁለት ሴት አትሌቶች ድል ቀንቷቸዋል፡፡

በሁለቱም ፆታዎች ኢትዮጵያውያን የበላይ የሆኑበት የ2016 ሀምቡርግ ማራቶን

በ2016 ሀምቡርግ ማራቶን መሰለች መልካሙ በሴቶች የውድድር ስፍራውን ሪኮርድ ከሁለት ደቂቃ በላይ በሆነ ግዜ በማሻሻል ጭምር ስታሸንፍ የወንዶቹን ፉክክርም ኢትዮጵያዊው ተስፋዬ አበራ በበላይነት ጨርሷል፡፡

በሀይለኛ ንፋስ ታጅቦ በተከናወነው የዘንድሮው ሀምቡርግ ማራቶን የሴቶች ፉክክር ኢትዮጵያዊቷ መሰለች መልካሙ ከ20ኛው ኪሎ ሜትር በኋላ ለብቻዋ ተነጥላ በመውጣት በማራቶን ውድድር ተሳትፎዋ ሶስተኛው ፈጣን ሰዓቷ በሆነው 2፡21፡54 በአንደኛነት አጠናቃለች፡፡ ያለፈው ዓመት የአሸናፊነት ክብሯን ለማስጠበቅ የተወዳደረችው ኢትዮጵያዊቷ መሰረት ሀይሉ በመሰለች በሰፊ ልዩነት ተቀድማ በ2፡26፡26 ሁለተኛ ሆና ስትጨርስ የራሷን ምርጥ ሰዓት ከስምንት ደቂቃ በላይ ያሻሻለችው ጀርመናዊቷ አንያ ሸርል በ2፡27፡50 የሶስተኝነቱን ደረጃ ወስዳለች፡፡

ከሀምቡርግ ማራቶን ድሏ በኋላ በሰጠችን አስተያየት ‹‹ጥሩ ለመሮጥ ብመኝም ውድድሩ በጣም ከባድ ነበር፡፡ የተወዳደርነው ብርቱ ንፋስ እና ቅዝቃዜ በነበረው የአየር ሁኔታ ውስጥ ነው፡፡ ውድድሩ ከተጠናቀቀ በኋላ የአየር ሁኔታው ጥሩ ቢሆን ኖሮ ከዚህ የተሻለ ሰዓት ማስመዝገብ እችል እንደነበር ተገንዝቤያለሁ፡፡ በቀጣይነት ምን ላይ ማተኮር እንደሚኖርብኝ የቦስተን እና ለንደን ማራቶን ውድድሮችን አይቼ እወስናለሁ›› ያለችው መሰለች በሀምቡርግ ያሸነፈችበት ሰዓት ሪዮ ላይ ኢትዮጵያን በማራቶን ለመወከል ሊያበቃት እንደሚችል ተስፋ የምታደርግ ሲሆን ይህ ባይሳካ ከዚህ በፊት በብርቱ ተፎካካሪነቷ በምትታወቅበት 10000ሜ. ሚኒማ አሟልታ ወደሪዮ ለማቅናት በርትታ እንደምትሰራ ይጠበቃል፡፡

በወንዶቹ ፉክክር ባለፈው ጥር ወር የዓመቱ ፈጣን በሆነ 2፡04፡23 ሰዓት የዱባይ ማራቶን አሸናፊ ለመሆን የበቃው ኢትዮጵያዊው ተስፋዬ አበራ በሀምቡርግ 2፡06፡58 በሆነ ሰዓት በአንደኝነት አጠናቆ የውድድር ዓመቱ ሁለተኛ የማራቶን ድሉን አስመዝግቧል፡፡ ኬንያውያኑ ፊሊሞን ሮኖ (2፡07፡20) እና ጆሴፋት ኪፕሮኖ (2፡10፡44) በቅደም ተከተል ሁለተኛ እና ሶስተኛ ወጥተዋል፡፡ የቅርብ ተፎካካሪው የነበረውን ኬንያዊ አትሌት በመጨረሻዎቹ ሁለት ኪሎ ሜትሮች ውስጥ በማስለቀቅ ለአሸናፊነት የበቃው ቁመተ ሎጋው ተስፋዬ የውድድሩ አዘጋጆች ለዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማሕበር ባደረሱት ዘገባ ላይ በሰጠው አስተያየት ‹‹ውድድሩ እንደተጀመረ ብዛት ያለን አትሌቶች በመሪነቱ ስፍራ አንድ ላይ እየሮጥን ፈጣን ሰዓቶችን ማስመዝገብ ችለን የነበረ ቢሆንም ወደመጨረሻ አካባቢ የመሪነቱን ስፍራ ስይዝ የነበረው ሀይለኛ ንፋስ ፈትኖኛል›› ያለ ሲሆን በሪዮ ኦሊምፒክ ኢትዮጵያን ለመወከል ስላለው ዕድል ሲጠየቅም ‹‹ዋናው ነገር መራጮቹ የመጨረሻውን ውሳኔ የሚያሳልፉት መቼ ነው የሚለው ቢሆንም እስካሁን ባለው ሁኔታ ፈጣኑን ሰዓት ያስመዘገብኩት ኢትዮጵያዊ አትሌት እኔ ነኝ›› ብሏል፡፡

የሪዮ ኦሊምፒክ ጥቂት ወራት ብቻ በቀሩት በዚህ ሰሞን የሚካሄዱት የማራቶን ውድድሮች ላይ ተሳታፊ የሚሆኑ አትሌቶች በሙሉ በውድድሮቹ ላይ የሚፎካከሩት ከማሸነፍ በዘለለ በኦሊምፒክ ጨዋታዎቹ ላይ ሀገራቸውን ወክለው ለመቅረብ የሚያበቃቸውን ሰዓት የማስመዝግብ ግብን ጭምር አንግበው ነው፡፡

ሻሾ ኢንሰርሙ የናጋኖ ማራቶን የሴቶች አሸናፊ ሆናለች

በዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፈዴሬሽኖች ማሕበር የብር ደረጃ የተሰጠውና በጃፓን ዘንድሮ ለ18ኛ ግዜ በተከናወነው የናጋኖ ማራቶን የሴቶች ፉክክር ኢትዮጵያዊቷ ሻሾ ኢንሰርሙ በ2 ሰዓት ከ34 ደቂቃ ከ14 ሰከንድ አሸናፊ ሆናለች፡፡ አስቸጋሪ ንፋስ በነበረበት በዚህ ውድድር ሻሾ ለድል የበቃችው ከ40ኛው ኪሎ ሜትር በኋላ ወደፊት በመምጣት ሲሆን የፔሩዋ ግላዲስ ቴጄዳ (2፡34፡54) እና ካኦሪ ዮሺዳ (2፡35፡14) ሁለተኛ እና ሶስተኛ ወጥተዋል፡፡ ሻሾ በናጋኖ ያስመዘገበችው ውጤት እልፍነሽ አለሙ በ200 ዓ.ም. እና ፋጡማ ሮባ በ2004 ዓ.ም. ካስመዘገቡት ቀጥሎ በኢትዮጵያዊት አትሌት ስም የተመዘገበ ሶስተኛው ድል ሆኗል፡፡

በወንዶቹ ፉክክር ጃሪየስ ቻንቺማ በ2፡15፡31 ቀዳሚ ሆኖ ሲጨርስ ሞንጎሊያዊው ሰር-ኦድ ባት-ኦቺር (2፡15፡56) እና ጃፓናዊው ታዪጋ ኢቶ (2፡16፡32) ተከታዮቹን ደረጃዎች ይዘው አጠናቀዋል፡፡

አብራራው ምስጋናው በፖላንድ ዶዝ ሎድዥ ማራቶን አሸንፏል

Abrar.jpg

አብራራው ምስጋናው ውድድሩን በድል ሲያጠናቅቅ (Sportografia.pl/organisers) © Copyright

በዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፈዴሬሽኖች ማሕበር የብር ደረጃ በተሰጠውና በፖላንድ ሎድዥ በተካሄደው የዶዝ ሎድዥ ማራቶን የወንዶቹ ፉክክር ኢትዮጵያዊው አብራራው ምስጋናው በ2 ሰዓት ከ13 ደቂቃ ከ24 ሰከንድ ቀዳሚ ሆኖ ጨርሷል፡፡ ከፍተኛ እርጥበት ባዘለ አስቸጋሪ የአየር ሁኔታ ውስጥ በተካሄደው በዚህ ውድድር ኬንያውያኑ ሮጀርስ ኪፕቺርቺር እና ሙታይ ኪፕኬሜይ አብራራውን በመከተል ሁለተኛ እና ሶስተኛ ወጥተዋል፡፡

ኬንያዊቷ ራቼል ሙቱጋ የሴቶቹን ፉክክር በ2፡31፡41 በቀዳሚነት ስትጨርስ ፖላንዳዊቷ አግኔስካ መርዥዌስኪ (2፡32፡04) እና ቤላሩሳዊቷ ናታሲያ ኢቫኖቫ (2፡34፡47) ተከታዮቹን ደረጃዎች ወስደዋል፡፡

                   


Save for Later/ በኋላ ለማንበብ ያስቀምጡ
   
Up vote :20     Down vote :0     Ajeb vote :20

    Ajebnew Email

    Subscribe to ajebnew email for daily, weekly and/or monthly feeds and everything worth your time will be right in your inbox!


    WE ARE STORYTELLERS. BE SURE TO NEVER MISS ANYTHING.