Top

18

ፓትርያርክ ማትያስ:- ከፖፕ ፍራንሲስ ሊማሯቸው የሚችሏቸው ነገሮች

Wednesday 2nd of March 2016 04:50:00 AM  |  Deje Selam

Francis_Mathias.jpg (ማርች 2/2016/ የካቲት 23/2008 ዓ.ም):- የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ወደ ቫቲካን ጉዞ ማድረጋቸው እና ከሮማማው ፓፓ “ፖፕ ፍራንሲስ” ጋር ተገናኝተው መወያየታቸው በመገናኛ ብዙኃን ተዘግቧል፡፡ ሲጨባበጡ፣ ትከሻ ለትከሻ ተሳስመው ሰላምታ ሲለዋወጡ፣ ፓትርያርካችን ለፖፕ ፍራንሲስ ማስታወሻ መስቀል እና መጽሐፍ ሲሰጡ ሁሉ አይተናል። የሁለቱ መሪዎች ዋነኛ የመወያያ ርዕሰ ጉዳይ በመካከለኛው ምስራቅ ያለው የክርስቲያኖች መከራ፣ ስደትና የቤተ ክርስቲያን ውድመት እንደሆነ ከፖፑ ንግግር መረዳት ይቻላል። “የክርስቲያኖች የሰማዕትነት ደም የክርስትና ዘር ነው” የሚለውን ታዋቂ ቃል አንስተው ፖፑ ማብራራታቸው ተዘግቧል። ዝርዝሩን መመልከት ለሚሻ ዜናው ወደተዘገበባቸው ሥፍራዎች ጎራ ማለት ይችላል።

ሁለቱም መሪዎች ከተሾሙ ብዙም አልቆዩም። ፓትርያርክ ማትያስ February 28/ 2013፤; ፖፕ ፍራንሲስ ደግሞ    በቀናት ልዩነት March 13/ 2013 ነው የተሾሙት። ሁለቱም መሪዎች በአማኞቻቸው የሚታዩበትን ጠባይ በአጭር ጊዜ ለመቅረጽ የቻሉ ሆነዋል። ያሳዩት ጠባይ ግን ልክ እንደ ልብሳቸው እጅግ የተቃረነና የተለያየ ነው። ፓፓ ፍራንሲስ ልጆችን በማባለግ እና በሌሎችም አስነዋሪ ተግባራት ስሟ የጎደፈውን የካቶሊክን ቤተ ክርስቲያን በጥቂት ዓመታት ውስጥ ስሟን ለማደስና በዓለም ሕዝብ ዘንድ ያላትን ተቀባይነት እጅግ በላቀ ደረጃ ከፍ ለማድረግ ችለዋል። ፓፓው ከሠሯቸው ተግባራት መካከል አንዱ ለረዥም ዘመናት ተለያይተው የነበሩትን ኩባንና አሜሪካንን ለማስታረቅ ድልድዩን ያበጁትና ታሪክ የሠሩት እርሳቸው መሆናቸው ነው። ኮሚኒስቱን የኩባ አስተዳደር ከደመኛ “ኢምፔሪያሊስት ጠላቱ” ከአሜሪካን መንግሥት ጋር ለማግባባትና በሁለቱ ሕዝቦች መካከል የፈረሰውን የግማሽ ምዕት የግንኙነት መስመር ለመጠገን ችለዋል። ከዚህም በላይ ፓፓው በዓለም አማኝም ኢ-አማኒም ሕዝብ ዘንድ ሞገስ ያሰጣቸው ለድሀውና ለዝቅተኛ ኑሮ ለሚኖረው ለመላው የዓለም ሕዝብ ያሳዩት ጥብቅና፤ ገንዘብ አምላኪውን የዘመናችንን ሉላዊ ሥርዓት በይፋ እየተቃወሙ ለአገሮች ኢኮኖሚያዊ ጤንነት ያሳዩት ወገንተኝነት ነው። ድህነትን እንደበሽታ ለሚጠየፉ ብዙ ቅንጡዎች እና ቅምጥሎች ትልቅ ትምህርት በሚሰጠው ተግባራቸው ከኦባማ ዋይት ሐውስ እና የአሜሪካ ኮንግረስ እስከ ደቡብ አሜሪካ የተለያዩ  አገሮች ግድ የለሽ መንግሥታት ድረስ ምክራቸውን እና ተግሳጻቸውን አሰምተዋል። የቅምጥል ኑሮን የሕይወታቸው መመሪያ በማድረግ ረገድ ከዓለማውያኑ የባሱት መንፈሳውያን የእምነት መሪዎች በሆኑበት በዚህ ዘመን ፖፕ ፍራንሲስ የቫቲካንን ወደር የለሽ የድሎት መኪናዎች ለመጠቀም አሻፈረኝ በማለት እና እዚህ ግቢ የማትባል የግል መኪናቸውን በመጠቀም በንግግራቸውም በግብራቸው ቅምጥልነትን አውግዘዋል። Francis_2.jpg ለጉብኝት በሑዱባቸው አገሮች በአጃቢ የተሸለሙ መኪኖቻቸወን በማቆም እና በመንገድ ላይ ከሚጠብቃቸው ሕዝብ ጋር በተለይም ከሕጻናት እና የተለያየ በሽታ ካለባቸው ሰዎች ጋር በመገናኘት፣ እንኳን ለመንካት ለማየት እጅግ የሚፈትን በሽታ ያለባቸውን ሰዎች ሳይጸየፉ በማቀፍና ርኅራኄ በማሳየት ብዙዎችን አስደምመዋል። ሌሎችንም የታዘብናቸውን ብዙ ተግባሮቻቸውን መጥቀስ ይቻላል። ለዚህ ፅሑፍ ሲባል በዚሁ እንግታውና የኛው ፓትርያርክ ሊሟሯቸው ስለሚችሏቸው ነገሮች እናንሣ። መቸም አንድ የኦርቶዶክስን አባት ከካቶሊክ መሪ “ይህንን ተማር፣ ይህ መልካም የሆነ የኮቶሊኩ መሪ ተግባር ነው” ማለት ችግር ላይ ሊጥል የሚችል ነገር እንደሆነ ይታወቃል። “ካቶሊኮችን ያመሰግናሉ” የሚል የነገረ ሰሪ ጥላሸት ሊያስቀባም ይችላል። በቀድሞው ዘመን ቢሆንማ “ሰዎቹ ኮተሎኩ” ሊያሰኝም ይችል ነበር። ይሁን እንጂ ቅ/ያሬድ ከዚያች ትል መውደቅንና መነሣትን ተምሮና ተገንዝቦ፣ ሕይወቱን አርቆ ለቤተ ክርስቲያናችን ዓይን እንደሆነ ሁሉ የሰው ልጅም በሥላሴ አርአያ ከተፈጠረ ከሌላው ሰው (አማኝም ሆነ የማያምን፤ ኦርቶዶክስም ሆነ ካቶሊክ) መማር መቻሉ ያስመሰግነዋል እንጂ አያስነቅፈውም። ከባዶ ግብዝነትም ያድነዋል። ወደ ቀደመ ነገራችን ስንመለስ …. ከላይ እንዳየነው ፓትርያርክ ማትያስ ከፖፕ ፍራንሲስ በቀናት ልዩነት ነው የመሪነት መንበር የተቀበሉት። ነገር ግን በነዚህ 3 ዓመታት ምን ሠሩ ብለን ብንገመግም ከፀብና ከዓምባ ጓሮ፣ በአደባባይና በሚዲያ ከሚሰጡት አሸማቃቂ ንግግር ባለፈ እንዲሁም ከቅ/ሲኖዶስ አባላት በመራቅ ቤተ ክርስቲያንን ተደራጅተው ከሚዘርፉ ሰዎች ጋር ከመወዳጀት ሌላ መልካም ስም ያተረፉ አይመስለንም። የካቶሊኩ ፓፓ ለድሆች ጠበቃ መሆናቸውን አይተናል። የኛዎቹም ለኢትዮጵያ ድሃ ሕዝብ ጠበቃ ሊሆኑ ይገባቸው ነበር። በኑሮ ውድነት፣ በአስተዳደር ብልሹነት፣ በስግብግበነት መሬቱን እና ቤቱን እየተዘረፈ ትዳሩ ለሚፈርሰው ወገናቸው ጠበቃ ሊሆኑ ይገባ ነበር። ጋሻ ጃግሬዎቻቸው እርስበእርስ በመሸላለምና የቤተ ክርስቲያን ገንዘብ በገፍ በመዝረፍ በተጠመዱበት በዚህ ጊዜ “ኧረ ተዉ!!!” የሚል የአባት ተግሳጽ ሊያሰሙ ይገባ ነበር። እንደ ካቶሊኩ ፓፓ አስታራቂ እና የተበተኑትን ሰብሳቢ መሆን ቢያቅታቸው የተሰበሰቡትን ለመበተን መትጋት ግን አይገባቸውም ነበር። በዚህ አንድ ዓመት በማኅበረ ቅዱሳን ላይ የፈጸሙትና እየፈጸሙት ያለው ተግባር ብቻ ለታሪካቸው ትልቅ ጠባሳ እንደሚሆን ሊገነዘቡት በተገባ ነበር። በመካከለኛው ምስራቅ ለሚገደሉ ክርስቲያኖች አዝነው ሮም ድረስ እንደሔዱት ሁሉ፣ በአገራቸው ለሚጠፋው ሕዝባቸው፤ በመንግሥት ወታደር ዕለት ከዕለት እየተገደለ በየጥሻው ለሚጣለው ወገናቸው፤ ማዕከላዊን ጨምሮ በየእስር ቤቱ በማሰቃያዎች ለሚንገላታው ወገናቸው ጠበቃ መሆን ይችሉ ነበር። ድሃ አደጉንና ዕጓለ ማውታውን ለመሰብሰብ ከአበው ሌላ ማን ይመጣል። ቤተ ክህነቱ ከገባበት አስረሽ ምቺው ተላቆና የምንኩስና አሰረ ፍኖቱን ተከትሎ ከዚህ የመንደላቀቅና የመሽቀርቀር አዚም ሊገላገል፣ ለድሃውም ሊያዝን ይገባው ነበር። የካቶሊኩን ፓፓ ካነጋገሩ አይቀር ይህንን ይህንንም ከእርሳቸው ይማሩ። ፓትርያርካችን ሆይ! በእርስዎ ዘመን ቤተ ክርስቲያናችን ስሟና ታሪኳ ይገነባል ወይስ ይፈርሳል?       ቸር ወሬ ያሰማን አሜን

                   


Save for Later/ በኋላ ለማንበብ ያስቀምጡ
   
Up vote :18     Down vote :0     Ajeb vote :18

    Ajebnew Email

    Subscribe to ajebnew email for daily, weekly and/or monthly feeds and everything worth your time will be right in your inbox!


    WE ARE STORYTELLERS. BE SURE TO NEVER MISS ANYTHING.