Top

18

ከ”አሜን ባሻገር”ን በዐይነ-ደብተራ አሻግረን ባየናት ጊዜ!

Tuesday 15th of March 2016 10:17:00 PM  |  Deje Selam

KeAmen%2BBashager%2Bcover.jpg (በአማን ነጸረ በፌስቡክ እንደጻፉት):- መጽሐፊቱ ጓዘ-ብዙ ናት፡፡ ታሪክ፣ፖለቲካ፣የጉዞ ማስታወሻ ትነካካለች--መጽሐፊቷ፡፡ የታሪክ ማጠንጠኛዋ አጼ ምኒልክን ማዕከል ያደርጋል፡፡ ጭብጧ “አጼ ምኒልክ ያገሪቱን ማዕከላዊና ደቡባዊ ክፍል እስከ ጠረፉ ባስገበሩበት ጊዜ ከብሔር ብሔረሰቦች ቀደምት አበው፡- የሌላውን ብሔር ያልተነኮሰ፣በራሱ የብሔረሰብ አባላት ላይ ኢ-ሰብአዊ ድርጊት ያልፈጸመ፣በውስጡ ዲሞክራሲያዊ አስተዳደር ያሰፈነ የብሔር ወይም የጎሳ ባላባት ያለው ብሔረሰባዊ ምሁር የምኒልክን አጽም በድንጋይ ይውገር” የምትል ሆና ተሰምታኛለች፡፡ መከራከሪያው ቅጣት ማቅለያ ይሆን እንደሆነ እንጅ አንዱ ብሔር በሌላ ብሔር ተወላጅ ባላባት ሲጨቆንና በራሱ ቋንቋ ተናጋሪ ብሔረሰብ ሲጨቆን ስሜቱ እኩል አይመስለኝም፡፡ በዚህ ላይ ያለነው ብሔር-ተኮር ክልላዊ አረደጃጀትና ሕገ-መንግሥታዊ ቁመና በገነነበት ጊዜ ነውና የጨቋኙ ብሔረሰባዊ ማንነትም ለወገናዊ ትረካው አስተዋጽኦ አለው ብዬ አምናለሁ፡፡  ዞሮ ዞሮ የምወደው በዕውቀቱ በጉዳዩ ጭንቅ ገብቶት እንደ አንድ ኃላፊነት ያለበት ወጣት ደራሲ የሚሰማውን ባነበበው ልክ አዋዝቶ መጻፉ አያስከፋኝም፤እንኳን ጻፈ!የ”ያገባኛል ስሜት” ያንጻል እንጂ አያናውጽም፡፡ ቢናወጸም ንውጽውጽታውን አረጋግቶ ማጽናት የባለሙያዎቹ ሥራ ነው፡፡ በበኩሌ በዚህ ጉዳይ ከዚህ በላይ ማለት አልችልም፡፡ አነሳሴም እንዲያ አይደለም፡፡ ከመንፈሳዊ ጉዳዮች ጋር በተነሱ ርእሶች ብቻ ከአሜን ባሻገርን አሻግሬ ለማየት እሞክራለሁ--በዐይነ-ደብተራ፡፡

 በእይታዬ ስሜታዊ የሆንኩ አይመስለኝም፡፡ የሰለቸኝን በተጻራሪነት ተሰልፎ የ”ልክ ልኩን ንገረው” መንገድ አልተከተልኩም፡፡ በቲፎዞነት ቆሞ “ወያላው ዝም” ዘይቤም አልተከተልኩም፡፡ ሳነብ የተሰማኝን እንደወረደ አቀርባለሁ፡፡ እይታዬ 3 አዝማች አርእስት አሉት፡፡ እነሱም፡-
 1. ከአሜን ባሻገር፡- አዳራሽ እና ቤተመቅደስ!
 2. ከአሜን ባሻገር፡- ባይካተቱ የምላቸው አገላለጾች
 3. ከአሜን ባሻገር፡- ያልተሻገራቸው ጥቂት የግዕዝ ቃላት ግድፈቶች


1. አዳራሽ እና ቤተመቅደስ!


1.1. አዳራሽ፡- በግዕዝ ቋንቋ ያለው መጠሪያ!


በግዕዛችን “አዳራሽ” የሚለውን ቃል ለመግለጽ የሚያገለግሉ በእኔ ትውስታ እንኳ 5 ስያሜዎች አሉ፡፡ (1) መርጡል፡- መርጡለ-ማርያም ስንል የማርያም አዳራሽ ማለት ነው፡፡ (2) ተሥላስ፡፡ (3) ማኅፈድ፡፡ (4) ጽርሕ፡- ጽርሐ-አርያም ወይም ጽርሐ-ንግሥት ወይም ጽርሐ-ፓትርያርክ ስንል በሁሉም ቃላት ውስጥ ያለው የጽርሕ ትርጉም አዳራሽ ነው፡፡ (5) ታዕካ፡- ታዕካ-ነገሥት ስንል የነገሥት አዳራሽ ማለት ነው፡፡ በእነዚህ ቃላት ውስጥ፡- መርጡል፣ጽርሕ እና ታዕካ የሚሉ ቃላት የአብያተ-ክርስቲያናት ቅጽሎች ናቸው፡፡ ትርጓሜያቸው “አዳራሽ” ነው፡፡ ታዲያ እየተስተዋለ!ትርጉምና መጠሪያ ይለያያል!ትርጉም አንድምታ/ትንታኔ/ሐተታ ነው!


1.2. አዳራሽ፡- በመጽሐፍ እና አንድምታ!


በማርቆስ ወንጌል 14 ቁ 13 ጌታ ደቀመዛሙርቱን የመጨረሻውን እራት በጸሎተ-ሐሙስ እንዲያሰናዱለት ትእዛዝ ሲሰጥ “በደርብ ላይ ያለውን የተሰናዳና የተነጠፈ ታላቅ ‹አዳራሽ› ያሳያችኋል፤በዚያ አሰናዱልን” ይላል፡፡ በቅዳሴ ማርያም እመቤታችንን “ምስራቅ እፁት-ዘሕዝቅኤል” ይላታል አባ ሕርያቆስ፡፡ አበው ይሕን ምሳሌያዊ ገለጻ ሲያብራሩ “ሕዝቅኤል በጽኑ መቆለፊያ የተቆለፈች ‹አዳራሽ› ያየብሽ ምሥራቅ አንቺ ነሽ፡፡ ሕዝቅኤል ከምሥራቅ ወደ ምዕራብ ከቤተመቅደስ ሲገባ ታላቅ ‹አዳራሽ› በጽኑ መቆለፊያ ተቆልፋ … አይቷታል፡፡ ‹አዳራሽ› የእመቤታችን፣ቁልፍ የማኅተመ-ድንግልናዋ ምሳሌ …” ሲሉ ያመሰጥሩታል (ቅዳሴ ማርያም ንባቡና ትርጓሜው፡ገ.59)፡፡ አባ ሕርያቆስ አክሎም እመቤታችንን “ጽርሕ ንጽሕት ዘሚልክያስ” ይላታል፡፡ ትርጓሜው የሚልክያስ ንጽሕት አዳራሽ ማለት ነው፡፡ እየተስተዋለ!አዳራሾች ሁሉ እኩል አይደሉም!ሕዝቅኤልና የሚልክያስ አዳራሽ ተምሳሌታዊ ትርጉም ሌላ ነው!የኢሰማኮ እና አፍሪካ ሕብረት አዳራሽ ትርጉም ሌላ ነው!ተሰብሳቢውና የስብሰባው ምስጢርም ሌላ!ሌላ!በስም ቃላዊ ፍቺው ከመመሳሰሉ በቀር አንዱ ካንዱ የተለየ ነው--የቀደመው አዳራሽ ቅዱስ የሚል ቅጽል አለው፡፡


1.3 ስም እና ቅድስና!


ቅጽር-ቤተክርስቲያን የገባ እና የተገነባ ሁሉ ለእግዚአብሔር የተለየ ነው፤መለየቱ በስያሜው ይገለጻል፡፡ ቤተክርስቲያን የገባ መባዕ ሁሉ ይቀደሳል፡፡ መቀደስ ማለት መለየት ነው ቀጥተኛ ፍቺው፡፡ መቀደሱን ተከትሎ ስሙም ይቀየራል፡፡ ምዕመኑ በስሙ አይጠራም፤በክርስትና ስሙ ነው--ተለይቷላ ለፈጣሪው፡፡ ቤ/ክ የገባ ስንዴ ስሙ “መገበሪያ” ነው--ተለይቷላ!እንጨቱ የሰሞን እንጨት ይባላል--ተለይቷላ!በቧንባ ኮለል ብሎ ቤተመቅደስ የሚያመራው ውሃ ከመቅደሱ ሲደርስ ስሙ “ማይ” ነው፡፡ አስቀዳሾች ዲያቆኑን ማይ/ፀበል ስጠን ይላሉ እንጂ የተቀደሰበት ውሃ ስጠን አይሉም--ተለይቷላ፤ተቀድሷል፤ስሙ ተቀይሯል፡፡ በቁርባን ጊዜ ደሙን የምንቀበልባት ንዋይ ስሟ በቤታችን ያለው የሻይ ማማስያ ስም አይደለም፤ዕርፈ-መስቀል ትባላለች--በቅድስና ስለተለየች ስሟም ልዩ ነው፡፡ የቤተክርስቲያን መገልገያዎች ሁሉ እንዲህ ናቸው፤ቅጽሩ ውስጥ ሲገቡ ዓለማዊ ስማቸውን አውልቀው አዲስ ማንነት ይላበሳሉ--ልክ እንደ ምዕመኑ ልብ!


1.4 አዳራሽ እና ቤተመቅደስ!


በትውፊታችን እንደሚታወቀውና በፍትሐ ነገሥት አንቀጽ 1 እንደተመለከተው የቤተክርስቲያን ሕንጻ ተሠርቶ ሲጠናቀቅ ቢያንስ 7 ተራዳኢ ካሕናትና ዲያቆናት ያስከተለ ጳጳስ አዲሱን ሕንጻ እና በውስጡ ያሉትን ንዋያት ከነታቦቱ በሜሮን ያከብራል(ይቀባል)፡፡ በ4ቱም የቤ/ክ መዐዝናት ባሉ በሮች ዑደት በማድረግ ምስባክ ይሰበካል፣ወንጌል ይነበባል እንዲሁም ምልጣን እየተመራ ይዘመራል፡፡ ሥርዓተ-ዑደቱ እና ቡራኬው ሲጠናቀቅ ታቦቱ ገና በዕለቱ የገባ አዲስ ቤ/ክ ከሆነ የደብሩ እና የአስተዳሪው አለቃ ስያሜም ብዙ ጊዜ አብሮ በዕለቱ በተገኙት ጳጳስ ይሰየማል፡፡ ከዚያ በኋላ ሜሮን የተቀባው ሕንጻ ስሙ ቤተመቅደስ ይባላል፡፡ ቤተመቅደስ ማለት ማመስገኛ፣ጸሎት ማሳረጊያና መሥዋዕት ማቅረቢያ ማለት ነው፤ለእግዚአብሔር ተለይቶ የተቀደሰ ቤት--ቤተ መቅደስ፡፡ በውስጡ ያሉት መገልገያዎች ንዋየ-ቅድሳት፡፡ መቅደሱ የሰው መሰብሰቢያ እስከሆነ ድረስ “አዳራሽ” ቢባልስ የሚል ቢኖር “ባንዴራ ማለት ጨርቅ ነው” ያሉት መሪ ያገኛቸውን ጣጣ ወይም አንድ ወቅት በሐዋሳ ዪኒቨርሲቲ “ቁርዐን ማለት ወረቀት ነው” በሚል የተፈጠሩ እሰጥ አገባዎችን ወይም በ1997 ዓ.ም በነበረው ክርክር “ሕገ-መንግሥቱ ወረቀት ነው” የሚሉ ክርክሮች እንዴት እየተበለቱ ተናጋሪዎቹን ላልሆነ ትርጉምና ወቀሳ እንዳጋለጡ ያላስተዋለ ሰው ነው፡፡ ከዚህ አንጻር የምወደው በዕውቀቱ ሥዩም “አዳራሽ”ን የቤተመቅደስ ተለዋጭ ሥም አድርጎ መጠቀሙ በመርሕ ደረጃ ስሕተት ነው፡፡ ሆኖም የወንድ በር ደግሞ አንከለክለውም፡፡ መቋሚያችንን በቁጣ “ለይሑዳ ወልዱ ወውለደ ውሉዱ ይደምሰስ” ብለን ለመቀወር ከማንሳታችን በፊት እናስሾልከው!


1.5 የገድለ ቅዱስ ላሊበላ መግቢያ ለበዕውቀቱ የሰጠው የወንድ በር!


ከላይ የተጠቀሱት በግዕዝ ቋንቋ አዳራሽን ለመግለጽ የተቀመጡ ቃላት ቅጣት ለማቅለል ያህል ይሆኑ ይሆናል እንጂ የበዕውቀቱን ዳህጸ-ብዕር (የብዕር ሸርተቴ) ስርየት የሚያስገኙለት አይሆኑም፡፡ አሁን የማቀርባቸው ምክንያቶችም እንዲሁ ለመሹለኪያ ንጂ ለንጽሕና ማረጋገጫ አያግዙም፡፡ እንዲያም ሆኖ ደግሞ በዘራፍ-ሞቅታ እየተነሱ ልጁ ላይ በኢ-ሚዛናዊነት ውርጅብኝ የሚያዘንቡበትን ስልጡን ፈራጆች አሰላስለው እንዲናገሩ በመጎትጎት ለወንድማችን ፋታ ማግኛ የወንድ በር ከቅዱሱ ንጉሥ ገድል ላይ አግኝተንለታል፡፡ በ2003 ዓ.ም በደብሩ ሰበካ ጉባኤ አማካይነት በፕሮግረስ ማተሚያ ቤት በግእዝና አማርኛ የታተመው ገድለ ቅዱስ ላሊበላ በመግቢያው ገጽ 16 የቅዱስ ላሊበላን ሕንጻ በአድናቆት እያነሳሳ አንባብያኑን ለመንፈሳዊ ግብዣ ይጠራል፡፡ ለጉብኝት ሲጋብዝ በብዛት የሚጠቀመው ቃል “አዳራሽ” የሚለውን ነው፡፡ አብረን እንየው፡፡ “… በላሊበላ እጅ የተሠሩትን አብያተ-ክርስቲያናት ሕንጻ ያይ ዘንድ የሚወድ ሰው ቢኖር ይምጣ፤ባይኖቹም ላይ እንደ ሙሴ ድንኳን የላሊበላ ‹አዳራሾች› ሕንጻዎች የሚያረጁ አይደሉምና፡፡ የላሊበላ (ገብረ መስቀል) ‹አዳራሾች›ስ ኢየሩሳሌም ሰማያዊት እስክትታይ ድረስ አይነዋወጡም፤አይጠፉምም” ይላል፡፡ ይቺን የገድለ ቅዱስ ላሊበላ መግቢያ ያየ የበዕውቀቱ ኀያሲ ውግዘቱን ረገብ ያደርጋል ብለን እናምናለን፡፡ የወንድ በር ማለት ይሄው ነው!በዚህ ላይ በዕውቀቱ እኔ በአቅሜ ነቅሼ “የላስታ ገጸ በረከት” ከምትለዋ መጣጥፉ ለማውጣት እንደ ሞከርኩት አዳራሽ ከሚለው 9 ጊዜ መላልሶ የተጠቀመው ቃል በተጓዳኝ ሕንጻ የሚል ቃል ለ6 ጊዜያት፣ቤተክርስቲያን የሚል ቃል እንዲሁ ለ6 ጊዜያት፣እንዲሁም መቅደስ የሚለውን ቃል ለ5 ጊዜያት በተለዋጭነት ተጠቅሟል፡፡ የገድለ ላሊበላ መግቢያ በሰጠው መሹለኪያ ላይ እነዚህ ተለዋጭ ቃላት ሲታከሉ ፍርዱን ባያስቀሩለትም ያለዝቡለታል፡፡


2. ከአሜን ባሻገር፡- ባይካተቱ የምላቸው አገላለጾች!


የሳይኮሎጂ አስተማሪያችን በአንድ ንግግር ውስጥ 3 ነገር አለ ብሎን ነበር፡፡ ንግግር፣ተናጋሪና መናገሪያ፡፡ ለእነዚህ ለ3ቱ ያለን አመለካከት በመረዳት ፍላጎታችንና አቅማችን ላይ ተጽእኖ አለው፡፡ ተናጋሪውን መውደድና አለመውደድ በንግግሩ አረዳዳችን ላይ ተጽእኖ አለው፡፡ የንግግሩ ይዘት በራሱ አሉታዊና አዎንታዊ የአሰማም ጫና አለው፡፡ ለመናገሪያውን ሚዲያ ያለን አተያይ አረዳዳችንን ይቀርጸዋል፡፡ በኢቲቪ የሚነገር ሁሉ ማይዋጥለት አለ፤በኢሳት የተነገረ ሁሉ የሚያንገሸግሸው እንዲሁ፡፡ እኒህ ሰዎች ተናጋሪውንና ንግግሩን ሳይሆን መናገሪያውንም ፈርጀውታል፡፡ ወደ ወንድም በዕውቀቱ ስንመለስ ገና መጽሐፉ ሳይወጣ ርእሱ “ከአሜን ባሻገር” መሆኑን ሲያውቁ አስቀድመው ያወገዙ አጋጥመውኛል፡፡ ተናጋሪውን አልተቀበሉትም!ምዕናባዊ ጽሑፍና ተአምራዊ ጽሑፍን እያምታታ በአንዱ መነጽር አንዱን ያያል የሚሉም አሉ፡፡ እነዚህኞቹ ጋር ስላስማማ አልቀርም፡፡ ከማሳያ ጋር ላቅርባቸው፡፡


2.1. በዕውቀቱ በገጽ 25 “የላሊበላ አዳራሾች በቃላት ወይም በፊልም ለማስረዳት መሞከር አሪፍ ቅኔን በዱዳ ቋንቋ ለመተርጎም እንደ መሞከር ነው” ይላል፡፡ ይሕን የመሰለ ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥም አለ፡፡ ቅዱሱ መጽሐፍ “ሽባው ተተረተረ፤ዲዳው ተናገረ፤መጻጉዕ ተፈወሰ፤ጎባጣው ቀና፤ለምጻሙ ነጻ፤ዕውሩ አየ፤አንካሳው ዘለለ” ማለትን ያዘወትራል፡፡ የገድለ ላሊበላ ጸሐፊም ለቅዱስ ላሊበላ ያለውን አድናቆት “አንደበተ-ዲዳ ለሆንኩ ለእኔስ በጥበብም ሆነ በጽድቅ መልክ … ከመሬታውያን ሁሉ የከበረ የዚህን የከበረ ሰው ትሩፋቱን ሁሉ እጽፍላችሁ ዘንድ ተሳነኝ” ይላል (ገድለ ቅዱስ ላሊበላ፡ገ.269)፡፡ እነዚህ በቅዱሱ መጽሐፍና በገድሉ ውስጥ የሚገኙ ቃላትን መፋቅ/መቀየር አንችልም፡፡ አመለካከታችንና የቃላቱን አረዳድ ግን መቀየር እንችላለን፡፡ ይሄን ለመቀየር ደራሲያን ያላቸው አቅም አይታበልም፡፡ መቀየሩ የቃላቱን አጠቃቀም በድርሰት ሥራዎቻቸው ከዘመኑ በማጣጣም የሚጀምር ይመስለኛል፡፡ ከዚህ አንጻር በዕውቀቱ “ዱዳ” የምትለዋን ቃል ለማንጸሪያነት ባይጠቀም ጥሩ ነበር እላለሁ፡፡


2.2. የላሊበላ ተጓዥ ምዕምናን አንዱ ላንዱ “ተው ማርልኝ” እያሉ በጉዟቸው ወቅት የሚያቀርቧቸውን መንፈሳዊነት ያላቸውን አራኅራኅያን ዝማሬዎች በዕውቀቱ በገጽ 37 የገለጸበት ቋንቋ “ቅዱስ ላሊበላም በኒህ ዘፈኖች እየተዝናና በውክልና መማሩን ይቀጥላል” የሚል ነው፡፡ ይሕ ዐ/ነገር ይተንተን ቢባል ነገሩ ነገርን ይወልዳል፡፡ ያስቀይማል!ላሊበላን ከጎጃም መርጡለ-ማርያም አባይን በዋና እየተሻገሩ ከአንዴም ሁለት ጊዜ ላሊበላን ስመውና ቆርበው የተመለሱ አረጋውያን አያቶችን ዝማሬ በዕውቀቱ ሲጎደፍርብኝ ለአፍታ ቅሬታ አላደረብኝም ብዬ አልዋሽም፡፡ ምነ!ይቺን ዐ/ነገር ባላስገባት ብያለሁ!


2.3. በጥቅሉ ስለእግዚአብሔር እና በመጽሐፍ ቅዱስ ስላሉ አበው ያሰፈራቸው የተወሰኑ አገላለጾች አሉ፡፡ ለምሳሌ፡- የአቤልንና የቃኤልን መሥዋዕት በሚመለከት በገጽ 90 እግዜርን እንደ ጥሎሽ ተቀባይ የገለጸበት መንገድ፤እንዲሁም የእነ ኖኅንና ሎጥን የወይን ጠጅ ስካር ከኦሪቱ ወስዶ በገጽ 33 እነሱን ቀምቃሚዎች ማለቱ አንድም አነጋገሩ ከኢ-አማኒው በዕውቀቱ ስለሆነ ከመክበዱ በቀር የእውነት እርሾ ስላለው፣ሲቀጥልም የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮችን በሚመለከት ባለቤቶቹ ኦርቶዶክሳውያን ብቻ ስላልሆንን በተለየ መልኩ የጥቃት ስሜት አልተሰማኝም፡፡ ይልቅስ ያልወደድኩለትን 3 ተጨማሪ ማንጸሪያዎችን ላምጣ፡፡


2.4 “ይምርሃነ የሚባል ቅዱስ ንጉሥ ካላጣው ሜዳ እንደ ገመሬ ዝንጀሮ እዚያ ላይ የወጣበት ምክንያት ምንድን ነው?>> ሲል ይጠይቃል በዕውቄ በገጽ 162፡፡ ለንጽጽር የተጠቀመው ቋንቋ ደስ አያሰኝም፡፡ ደስ የማያሰኘው እሱ ስለተናገረውና ንግግሩ ሰምና ወርቅ ስለሌለው ነው፡፡ ንግግሩ ሰምና ወርቅ ኖሮበት አማኒ ሰው ቢናገረው ክፋት አይኖረውም ነበር፡፡ ላስረዳ፡፡ ቶማስ-ዘመርዐስ የተባለ በዘመነ-ሰማዕታት ስለዕምነቱ ጽናት በአላውያን ሕዋሳቱ በየቀኑ ይቆራረጡ የነበረ ሰማዕትን ተጋድሎ እና የአቡነ ተክለሃይማኖትን ለጸሎት በመቆም ብዛት ስብረተ-አጽም ማጋጠም የምትተረክ ቅኔ አብነት ትሁነን፡፡ ቅኔዋ በሰም ሰማዕቱ ቶማስን ዶሮ፣ጻድቁ ተክለሃይማኖትን ዶሮ ተመጋቢ አድርጋ ታስቀምጣለች፤በወርቅ ግን ተጋድሎአቸውን ነው የምታጠይቅ፡፡ ይቻትና፡-
 ተክለ-ሃይማኖት፡ይትፌሣህ፡በተጠብሆ-ቶማስ፡ዶርሖ፣
 ሐጺር፡እግር፡እስመ-ለተክለ-አብ፡በጽሖ፡፡
 ትላለች፡፡ ቀጥተኛ ትርጉሟ፡-ቶማስ ዶሮው ሲበለት ተክለ ሃይማኖት ደስ ይለዋል፤ለተክለ ሃይማኖት አጭር እግር ይደርሰዋልና የሚል ነው፡፡ ምስጢራዊ ትርጉሙ ግን ከላይ እንደተገለጸው ተጋድሎውን ነው የሚተርከው፡፡ ይሕ ቅኔ ተቀባይነት ያገኘው ተናጋሪው አማኒ በመሆኑና ቅኔውም ሲፈታ ወርቁ ጥሩ መልእክት ስላለው ነው፡፡ ይቺ ለኦርቶዶክሳዊው ባለቅኔ የተሰጠች መብት ለበዕውቀቱ አታገለግልም፡፡ መብቱ ወሰን አለው!ኢ-አማኒ ነኝ ካሉ በኋላ በአማንያን ቤት ዘው ብሎ መተንተን መዘዙ ብዙ!


2.5. በገጽ 237 የቀረበው የ”God Bless America” እና የ12 ጊዜ እግዚኦ መሐረነ ክርስቶስ ንጽጽር ከጊዜ አጠቃቀም አንጻር ማስፈገጉ ባይካድም ተጋፊነቱ ያይላል፡፡ ደህና ሲያስቀኝ የቆየው የደብረ ማርቆሱ ርዕሶም የድል አጥቢያ ተጋዳይነትና የቆየ ታጋይ መስሎ ራሱን ማዋደድ ገጽ 241 ሲደርስ “ከኪሱ ውስጥ የስዕለት ግምጃ የሚያክል መሀረም ጎልጉሎ አውጥቶ ከመጠን በላይ እየተናፈጠ በመጠኑ ያለቅሳል” የሚል ገለጻ በስዕለት ገንዘብ የሥዕለት ግምጃ የለበሰ መጽሐፍ ዘርግቼ እየተማርኩ ትምህርቱን ስጨርስ መጽሐፉን ከነግምጃው ስሜ ወንበር እያጠፍሉ ላደኩት የቄስ ልጅ ቅር የሚያሰኝ አገላለጽ ነውና እዚች መስመር ላይ ስደርስ ሳቄን ገታሁት፤አቆምኩት፡፡ ከዚያ መልሼ በዕውቀቱ “እንደ ቄስ በቅሎ በየገጹ አትቁም” ቢለኝስ  ብዬ በመስጋት ንባቤን ቀጠልኩ፡፡ በልቤ ግን ይሄ ቅብጢ እንዴት ወበራ!ሳልል አልቀረሁም!


2.6. ያም ሆኖ በገጽ 106 የስም መቀየር በተነሳ ቁጥር ቤተክህነትን ብቻ ነጥሎ መውቀስ እንደማይገባ ለማሳየት የቀድሞው ቱሉ እስልምናን ሲቀበል አባ ጅፋር መሰኘቱን፣የሳሆው (ኤርትራ) ሙስሊም የነበረው ግለሰብ ከእስልምና ወደ ፕሮቴስታንትነት ሲቀየር ሳሙኤል ጊዮርጊስ መባሉን አስረጂ መቁጠሩ ደስ አሰኝቶኛል፡፡ መጀመሪያ “ስም እና ማንነት” ለሚለው መጣጥፉ ቆሜ ማጨብጨቤን አልደብቅም!ብራቮ በዕውቀቱ ሥዩም በዳዳ ወዬሳ!ብዬ ነበር!ምን ያደርጋል!ገጽ 164 ላይ ስደርስ በዕውቄ “አሁን ሐረር ውስጥ ነኝ፡፡ የዛሬ መቶ ዓመት አባቶቼ በወራሪነት የረገጡበት ቦታ ላይ በቱሪስትነት ቆሜ ስለጦርነት ገጸ በረከቶች እያሰብኩ” ነው ሲል ራሱን ከተወራሪ ብሔር ተወላጅነት ወደ ወራሪ ወራሪ ተለወላጅነት ቀይሮ እዋ!አሰኘኝ!አሁን ተምንጊዜው ወራሪ ሆንሽ!ልለው ስል አባትነት በእናት ወገን በኩል ሊኖር ይችላል፤ወይም የሸዋ ኦሮሞ በሐረር ጦርነት ስለተሳተፈ የነ ኦቦ በዳዳ ወዬሳ ተሳትፎ በዚያ በኩል ሊኖር ይችላል ብዬ ራሴን ኄስኩ!በገጽ 169 እና 170 ስለመቻቻል ያነሳቸው ነጥቦችና ትዝብቶች ግነት በዝቶባቸዋል ብልም ስጋቱ ስጋቴ ነው!ለቢላደን ጺምና ለግራኝ መሐመድ ያለው አመለካከት ከተርታው ሕዝብ የተለየ ስላልሆነና የሮም ካቶሊካውያን ለብፁዕነት ያጨየዋቸውን አባ ማስያስ በገጽ 221 በዘረኝነት መክሰሱ ዘለፋው ለሁሉም ሃይማኖቶች በፍትሐዊነት ይዳረስ ለሚሉ ኀያስያን ማለዘቢያ ሳይሆነው አይቀርም፡፡ በግሌ የበዕውቀቱ ሌሎችን ሃይማኖቶች መተቸት በተወሰኑ ለኦርቶዶክሳዊ ምዕመን ተጋፊ ለሆኑ ጽሑፎቹ ስርየት ያስገኛል የሚል ዕምነት ባይኖረኝም ከገፋ ሁሉንም ይግፋ ለሚሉት ተቺዎቹ እነዚህን መስመሮች እጠቁማለሁ፡፡ ለምሳሌ፡- ገጽ 106፣107 እና 221፡፡


3. ከአሜን ባሻገር፡- ያልተሻገራቸው ጥቂት የግዕዝ ቃላትና ትርጉዋሜያት ግድፈቶች


በዕውቀቱ ትጉሕ መዛግብት አገላባጭ ይመስለኛል፡፡ ሲያገላብጥ ያገኛቸውን በግዕዝ ቋንቋ የተሰደሩ እምቅ ሐሳቦች ለመጽሐፉ ግብዐት በማዋሉ ደስ ብሎኛል፡፡ ሆኖም የበለጠ ደስ እንዲለኝ በሣልሳይ ኅትመቱ ውስጥ ቢያቃናቸው የምላቸውን ጥቂት የቃላት ግድፈቶች በቅንነት ልጠቁም፡፡
 3.1. ገጽ 62 ላይ በዕውቀቱ፡-
 “አመ-ሠላሳ፡ቀን፡ጎበና፡ባይፀና፣
 ይካፈሉን፡ነበር፡እነ፡ቱፋ፡ሙና፡፡ “
 ካለ በኋላ “አመ-ሠላሳ፡ቀን” ማለቱ ጦርነቱ የፈጀውን ጊዜ ለመግለጽ እንደሚመስለው ይጠቁማል፡፡ መሰለኙ አልሰራም፡፡ “አመ” የሚለው የግዕዝ ደቂቅ አገባብ “የ-” ወይም “-ጊዜ” ወይም “በ-” የሚል ትርጉም ነው ያለው፡፡ ስለዚህ “አመ-ሠላሳ፡ቀን” ማለት “የ30 ለታ” ወይም “የ30 ጊዜ” ወይም “በ30” የሚል ትርጉም ነው ያለው፡፡ አንድ ቀንን ያቺውም 30ኛዋን ቀን ብቻ ያመለክታል፡፡ መላውን ከ1 ጀምሮ እስከ 30 የሚደርሱ ቀናት አያመለክትም፡፡ ከዚሁ ተያይዞ “እግዚአብሔር፡ንጹሕ፡ባሕርይ፡ነው” ሲል የጠቀሰውን ቃል “እግዚአብሔር፡ንጹሐ-ባሕርይ፡ነው” ቢለው የቀና ይሆናል፡፡ ንፁሕ ባሕርይ የምትለዋን ንፁሐ-ባሕርይ ማለት!
 3.2. ገጽ 90 “ኦ አዛል ብእሲ ምንተ ያስተክዘከ(ምን ያስተክዘሀል?)” ሲል ያሰፈራት ጥቀስ “ኦ አዛል ብእሲ ምንት ያቴክዘከ”(አንቱ ብርቱ ሰው ሆይ!ምን ያስተክዘሀል?)” ቢባል የግዕዙን መልእክት ይሸከመዋል፡፡ ያስተክዘከ አይባልም፤ያቴክዘከ ነው፡፡
 3.3. ገጽ 146 ላይ የሰፈረችው ጉርድ መወድስ (ለዓለም) የመሰለች በዘመነ-አጼ ገላውዴዎስ ተደረገች ያላት ቅኔ ከመጠነኛ የፊደልና የትርጓሜ ስሕተት ውጭ ጥሩ ሆና ቀርባለች፡፡ እሷን አቃንቼ በዕውቄን እሰናበተዋለሁ፡፡ ቅኔዋ ከኋላ ያለው ማንጸሪያዋ ተጎርዶ እንደቀረ በደንብ ታስታውቃለች፤ጉራጁ ካለው ለቀጣይ ኅትመት ቢያሟላው ጥሩ ነው፡፡
 …ወለተ-ኢትዮጵያሰ፡ትትከደን፡አዕዳለ-ዘማዕስ፡ወአነዳ፣
 ወትለብስ፡ሰቀ፡ከመ-ሰሌዳ፣
 ወትዕንቅ፡ጋጋ፡ህየንተ-ሐብለተ-ወርቅ፡ዘውስተ-ክሳዳ፣
 ወህየንተ-ቤተ-ወይን፡ወማኅሌተ-ፅጌ፡እለ-ይላሁ፡ትረሲ፡ዐውዳ፣
 ወትክዐው፡ጸበለ፡ዲበ-ርእሳ፡ህየንተ-መዓዛ-ዕፍረት፡ወማየ-ጽጌረዳ፡፡
 ትላለች፡፡ የድሮ ቅኔ ስለሆነ ዜማ የጠበቀ አይደለም፡፡ ንጽጽሩና ሐሳብ አገላለጹ ግን በወቅቱ (በ16ኛው ክ/ዘ) ሀገራችን የነበረችበትን የሰቆቃ ኑሮ ሸጋ አድርጎ ይገልጻል፡፡ በዚህ ቅኔ ውስጥ በዕውቀቱ የገደፋቸውን ቃላት ለማውጣት ያህል፡- በመጀመሪያው መስመር ላይ “ኢትዮጵያሰ” ማለት ሲገባው “ኢትዮጵያስ” ብሎ ግዕዙን ወደ ዐማርኛ ጎትቶታል፡፡ ልዩነቱ “ስ” እና “ሰ” ነው፡፡ “ሰ” በስም መጨረሻ ስትገባ ያላት የግዕዝ ትርጉም “ግን/ነገር ግን” ማለት ነው፡፡ 4ኛው መስመር ላይ ያለው “ይላሕው” የሚል ቃል በዋናው መዝገብ እንዲያ ሊሆን ይችላል፡፡ ሆኖም በዘመናዊው ግዕዝ “ይላሁ” ቢባል ነው ሸጋ፡፡ 5ኛው ቤት ላይ “ደባለ” የምትለዋ ፊደል “ጸበለ” መባል ነበረባት፡፡ “ጸበል” ቀጥተኛ ትርጉሙ ትቢያ ማለት ነው--እሱም ጥሩ ተርጉሞታል፡፡
 ሰሌዳ የሚለው ቃል ትርጉም በዕውቀቱ በተዛማጅ ትርጓሜው እንዳመለከተው አይደለም፡፡ “ሰሌዳ” በግዕዝ የለሰለሰ ወይም ልዝብ ብራና(ሌዘር) ማለት ነው፡፡ ቃሉ አሉታዊ አይደለም፡፡ “ወትለብስ፡ሰቀ፡ከመ-ሰሌዳ” ሲባል “ልብስ በማጣቷ ሌዘር ይመስል ማቅ ለበሰች” ማለት ነው፡፡ የተቀሩትን ቁልፍ ቃላት ለመተርጎም ያህል፡-አዕዳል--ልብስ፡፡ ማዕስ--ያልለፋ ጀንዲ፡፡ አነዳ--ቁርበት፡፡ ሰቅ--ማቅ፡፡ የቀረውን ከበዕውቀቱ ተዛማጅ ትርጉም፡-
 የኢትዮጵያ ልጅ፤ቁርበት ደርባ፣
 እንደ ሰሌዳ፤ማቅ ተከናንባ፣
 በወርቅ ድሪ ሐብል ፋንታ፤አንገቷ ቀንበር ጠልቆላት
 የዘፈን ቤቷ ፈርሶ፣
 አደባባይዋ በለቅሶ፣
 የትካዜ ጭጋግ ለብሶ፣
 በሽቶ መዓዛና በጽጌረዳ ፈሳሽ ፋንታ
 በገጽዋ ትቢያ ነስንሶ፡፡
 ይለናል በዕውቀቱ ሥዩም፡፡ በአጠቃላይ በዕውቀቱ ኢ-አማኒ ነኝ ካለ ወዲህ በአማንያን አይን የሚኖረው እይታ እንደ ድሮው ስላልሆነ የሚጠበቅበት ጥንቃቄ መክበዱን ማስተዋል ይገባዋል፡፡ አመክንዮና ሃይማኖት የሚነጻጸሩበት መነጽር እየቅል የሚሆንበት ጊዜ አለና መስመሩን ላለማምታት ቢጥር ሸጋ ነው፡፡ ከወዲህ ደግሞ ሥራውን ከመተቸት ይልቅ ሰብዕናውን ማዕከል ያደረጉ “በድፍረቱ፣በውሸቱ፣666ቱ፣ሞሳዱ…” የመሳሰሉ ሃይማኖታዊ ካባ የተጎናጸፉ ስድቦችን የሚያስወነጭፉ ወንድም/እኅቶች ከተራ ስድብ እና ፍረጃ ድርደራ እንዲሁም “ከቁንጫ መላላጫ” አይነት ግልብ ኂሶችን ከመስጠት ይልቅ ጠቅላላ የጽሑፉን ዐውድ በማገናዘብ ምግባር ያልተለየው ኂስ ቢሰጡ ደስ ይለኛል፡፡ እከዚያው ግን በዕውቀቱ ሥዩም ለኢ-አማኒነት አበቃኝ ያለውን ጽሑፍ ለመዳሰስ ከአሜን ባሻገርን ትተን በዚህ http://www.pdf-archive.com/2014/10/19/sigmund-freud-the-future-of-an-illusion/sigmund-freud-the-future-of-an-illusion.pdf በኩል ተሻገረናል፡፡

                   


Save for Later/ በኋላ ለማንበብ ያስቀምጡ
   
Up vote :18     Down vote :0     Ajeb vote :18

    Ajebnew Email

    Subscribe to ajebnew email for daily, weekly and/or monthly feeds and everything worth your time will be right in your inbox!


    WE ARE STORYTELLERS. BE SURE TO NEVER MISS ANYTHING.