FUN /

Top

20

በዙሪኩ የዳይመንድ ሊግ ፍፃሜ በወንዶች 5000ሜ. የኢትዮጵያውያን የእርስ በርስ ፉክክር ይጠበቃል

Wednesday 31st of August 2016 12:59:42 PM  |  Ethio Tube

14199593_10154502012648637_1063684772104

ሙክታር እድሪስ – ዮሚፍ ቀጄልቻ እና ሐጎስ ገብረሕይወት ለሶስት ሽልማቶች ይፎካከራሉ

ከግንቦት ወር መጀመሪያ አንስቶ በአራት የተለያዩ አህጉራት በአስራ ሁለት የተለያዩ ከተሞች የተካሄደው የ2016 ዓ.ም. የዳይመንድ ሊግ ውድድር የመጀመሪያው የፍፃሜ ፉክክር ነገ ምሽት በስዊዘርላንድ ዙሪክ ይከናወናል፡፡ ማራኪ ፉክክሮች እንደሚታዩበት በሚጠበቀው የዙሪኩ ዳይመንድ ሊግ ፍፃሜ ሰላሳ ዘጠኝ አትሌቶች የዋንጫ፣ የገንዘብ እና በቀጣዩ ዓመት ዓለም ሻምፒዮና ላይ የቀጥታ ተሳትፎ (ዋይልድ ካርድ) የሚያስገኘውን የአጠቃላይ አሸናፊነት ቦታ ይዘው የማጠናቀቅ ዕድሉ አላቸው፡፡
በሁለቱም ፆታዎች 16 የውድድር አይነቶች ፍፃሜ የሚያገኙበት የዙሪኩ ውድድር በወንዶች 5000ሜ. በነጥብ ደረጃ ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ያለውን ቦታ የያዙት ኢትዮጵያውያኑ ሙክታር እድሪስ፣ ዮሚፍ ቀጄልቻ እና ሐጎስ ገብረሕይወትም የዓመቱ የአጠቃላይ አሸናፊ ለመሆን የሚፎካከሩበት ነው፡፡ ሶስቱ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የፍፃሜውን ውድድር የሚጀምሩት ከዚህ በፊት ባስመዘገቧቸው ውጤቶች መሰረት ሙክታር በ30 ነጥብ፣ ዮሚፍ በ22 ነጥብ እንዲሁም ሐጎስ በ15 ነጥብ ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ያሉትን ደረጃዎች ይዘው ሲሆን በፍፃሜው የነጥብ የበላይነቱን ይዘው ለማጠናቀቅ ብርቱ ትንቅንቅ እንደሚያደርጉ ይጠበቃል፡፡ ሙክታር ዮሚፍን በስምንት ነጥብ ልዩነት እየመራው የሚገኝ እንደመሆኑ ዮሚፍ እርሱን ቀድሞት ቢጨርስ ሁለቱም በአጠቃላይ ነጥብ እኩል ይመጣሉ፡፡ ሆኖም የፍፃሜ አሸናፊነቱ ዮሚፍን የዳይመንድ ሊጉ የአጠቃላይ አሸናፊ የሚያደርገው ይሆናል፡፡ ከዘንድሮው የውድድር ዓመት ጀምሮ ተግባራዊ መሆን በጀመረው የአይ.ኤ.ኤ.ኤፍ ዳይመንድ ሊግ የፍፃሜ ውድድሮች የነጥብ አሰጣጥ መሰረት አንደኛ የሚወጣ 20፣ ሁለተኛ 12፣ ሶስተኛ 8፣ አራተኛ 6፣ አምስተኛ 4 እና ስድስተኛ 2 ነጥብ የሚያገኝ ይሆናል፡፡ በዳይመንድ ሊጉ የወንዶች 5000ሜ. የነጥብ ሰንጠረዥ ላይ በ10 ነጥብ በአራተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ኢብራሂም ጄይላን እና ኢማነ መርጋ እንዲሁም የኬንያ እና የዩናይትድ ስቴትስ ጠንካራ አትሌቶችም የውድድሩ ተሳታፊዎች ናቸው፡፡
ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በዙሪኩ የፍፃሜ ፉክክር በሴቶች 1500ሜ. ዳዊት ስዩም፣ በሱ ሳዶ፣ ጉዳፍ ፀጋዬ እና አክሱማዊት እምባዬ እንዲሁም በ3000ሜ. መሰናክል ሶፊያ አሰፋ እና እቴነሽ ዲሮ የሚወዳደሩ ቢሆንም በነጥብ የአጠቃላይ አሸናፊ ለመሆን በሚደረገው ፉክክር ውስጥ የሚጠበቁ አይደሉም፡፡
በወንዶች ምርኩዝ ዝላይ ፈረንሳዊው ሬኖ ላቪሌኒዬ፣ በሴቶች 200ሜ. ኔዘርላንዳዊቷ ዳፍኔ ሺፐርስ፣ በሴቶች 100ሜ. መሰናክል አሜሪካዊቷ ኬንድራ ሀሪሰን፣ በሴቶች ርዝመት ዝላይ የሰርቢያዋ ኢቫና ስፓኖቪች እና በሴቶች ዲስከስ ውርወራ ክሮሺያዊቷ ሳንድራ ፔርኮቪች ውድድሩን ከ20 ነጥብ በላይ በሆነ ልዩነት በመምራት ከወዲሁ አሸናፊነታቸውን ያረጋገጡ ሲሆን ሽልማታቸውን ለማግኘትም በዙሪኩ የፍፃሜው ውድድር ላይ ተሳታፊ መሆን ብቻ በቂያቸው ነው፡፡ የምርኩዝ ዝላይ ተወዳዳሪው ፈረንሳዊ ሬኖ ላቪሌኒዬ ዳይመንድ ሊጉ ከተጀመረ አንስቶ በየዓመቱ ክብሩን ሳያስደፍር ዘንድሮ ሰባተኛ ድሉን ለማስመዝገብ የተቃረበ ብቸኛ አትሌት ነው፡፡ አሜሪካዊው 400ሜ. ተወዳዳሪ ላሽዋን ሜሪት፣ ስፔናዊቷ ከፍታ ዘላይ ሩት ቤይታ እና አሜሪካዊው ስሉስ ዘላይ ክርስቲያን ቴይለር በቅደም ተከተላቸው መሰረት እየመሩ ካሉበት የ12፣ 14 እና 16 ነጥብ ልዩነት አንፃር በዙሪክ አሸናፊ የመሆን ዕድላቸው ሰፊ ነው፡፡ በሴቶች 1500ሜ. ኬንያዊቷ የኦሊመፒክ ሻምፒዮን ፌይዝ ኪፕጎን በስምንት ነጥብ ልዩነት ከምትመራት እንግሊዛዊቷ ላውራ ሙዪር የሚያደርጉት ፉክክርም ተጠባቂ ከሆኑት መካከል አንዱ ሲሆን ሁለቱም በአሸናፊነት ከጨረሱ የዓመቱ የበላይነታቸውን ያረጋግጣሉ፡፡ ሙዪር ኪፒዬጎንን ቀድማ ብትጨርስ በነጥብ ሁለቱም እኩል የሚመጡ ቢሆንም የፍፃሜው ውድድር አሸናፊ መሆኗ የዳይመንድ ሊጉ አሸናፊ እንድትሆን ያደርጋታል፡፡
በሴቶች 3000ሜ. መሰናክል ፓሪስ ላይ የዓለም ሪኮርድ በመስበር ጭምር የዳይመንድ ሊጉን የነጥብ መሪነት የተረከበችው የኦሊምፒክ ሻምፒዮኗ ትውልደ ኬንያዊት የባህሬይን አትሌት ሩት ጄቤት የዓለም ሻምፒዮኗን ኬንያዊት ሀይቪን ኪገን በአራት ነጥብ ልዩነት እየመራቻት ትገኛለች፡፡ ይህም የርቀቱ የዓመቱ የበላይ ሆኖ ለማጠናቀቅ በሁለቱ አትሌቶች መካከል ዙሪክ ላይ የሚደረገውን የፍፃሜ ፉክክር የሚያጠነክረው እና በጉጉት እንዲጠበቅ ያደረገው ሆኗል፡፡ በሴቶች 800ሜ. በሁለት ነጥብ ልዩነት እየተከታተሉ ባሉት ደቡብ አፍሪካዊቷ ካስተር ሴመንያ እና በብሩንዲያዊቷ ፍራንሲኔ ኒዮንሳባ መካከል የሚኖረው ፉክክርም ሌላኛው ተጠባቂ ነው፡፡

                   


Save for Later/ በኋላ ለማንበብ ያስቀምጡ
   
Up vote :20     Down vote :0     Ajeb vote :20





    Ajebnew Email

    Subscribe to ajebnew email for daily, weekly and/or monthly feeds and everything worth your time will be right in your inbox!










    WE ARE STORYTELLERS. BE SURE TO NEVER MISS ANYTHING.