Top

18

የአዲስ አበባ የትራንስፖርት ተስፋ

Monday 8th of August 2016 06:08:35 AM  |  Admas Trade and Economy

ዛይ ራይድ ሜትር ታክሲዎች፤ በመጪው ሳምንት ስራ ይጀምራሉ፡፡አዲስ አበባ ከኒውዮርክና ጀኔቭ ቀጥላ ሶስተኛዋ የዲፕሎማቲክ ከተማ ናት፡፡ እነዚህ ዲፕሎማቶችና ቱሪስቶች እንዲሁም የመዲናዋ ነዋሪዎች ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት ይፈልጋሉ፡፡ ከ15 ዓመት በፊት በጣት የሚቆጠሩ ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች ነበሩ፡፡ ዛሬ፣ ከ100 በላይ ሆነዋል፡፡ አዲስ አበባ መሃሏ ነው እንጂ በአራቱም አቅጣጫ ሲመለከቱ፤ “እውነት አዲስ አበባ ናት!” በማለት ያስገርማሉ - በሪል እስቴቶችና በግለሰቦች የተገነቡት ዘመናዊ መኖሪያ ቤቶች፡፡
የመዲናዋ ከፍተኛ ችግርና ራስ ምታት የሆነው የትራንስፖርቱ ጉዳይ ነው፡፡ መንግስት ታክሲዎች በቀጠና ተሰማርተው እንዲሰሩ አደረገ፡፡ ነገር ግን ችግሩ ባሰበት እንጂ አልተቀረፈም፡፡ ሐይገር ባስ አስመጣ፤ ችግሩ ግን ያው ነው፡፡ ቅጥቅጥ ቺኳንታዎች፣ ከፍተኛ የህዝብ ማመላለሻ አውቶብሶችና የሲቪል ሰርቪስ አውቶቡሶች በድጋፍ ሰጪነት እንዲሰሩ ተደረገ፡፡ ምንም ጠብ አላለም፡፡ በስራ መግቢያና መውጫ እንዲሁም በስራ ሰዓት ረዣዥም ሰልፎች መመልከት የዘወትር ልማድ ከሆነ ሰነባብቷል፡፡
ይህንን ችግር ለመቅረፍ አሁንም መንግስት አዲስ ነው ያለውን ዘዴ ቀይሷል፡፡ አንዱ ረዥም ርቀት ተጓዥ አውቶቡሶችን ማቅረብ ነው፡፡ ችግሩን ምንም ያህል አልቀረፉም እንጂ 50 አውቶቡሶች ስራ ጀምረዋል፡፡ ሌላው ዘዴ ደግሞ የታክሲ ማኅበራት ተደራጅተው ዘመናዊ ታክሲዎች እንዲያስገቡ ማድረግ ነው፡፡
በብርሃን ባንክ የገንዘብ ድጋፍ 750 ታክሲዎች ተገዝተው ከቀረጥ ነጻ ሊገቡ ነው ተብሏል፡፡ በዚህ በሁለተኛው ዘዴ በመሳተፍ ችግሩን ለመቅረፍና የበኩሉን ሚና ለመወጣት ያሰበ ወጣት፤ የአሜሪካና የሌሎች አገሮችን ልምድ ይዞ ብቅ ብሏል፡፡ የዛይ ራይድ መስራችና ዋና ሥራ አስፈፃሚ ወጣት ሀብታሙ ታደሰ፡፡ ዛይ ራይድ የሚሰራው በሶፍትዌር ነው፡፡ የታክሲ አገልግሎት የፈለገ ሰው www.zayride.com ገብቶ ታክሲ እንዲመጣለት ጥሪ ያደርጋል፡፡  አገልግሎት ፈላጊው በአገልግሎት መጠየቂያ ፎርም ላይ ስምና አድራሻውን ይጽፋል፡፡ ከዚያም ታክሲው በጂፒኤስ እየተመራ፣ ወዲያው በአድራሻው ከች ይላል፡፡ ዛይ፤ በዝዋይ ሐይቅ ደሴት ላይ የሚኖሩ ዜጎች መጠሪያ ነው፡፡ወጣት ሀብታሙ ባሌ ውስጥ በጎባ ከተማ ነው የተወለደው፡፡  በአራት ዓመቱ ወደ አዲስ አበባ መጥቶ ት/ቤት ገባ፡፡ እስከ 7ኛ ክፍል ከተማረ በኋላ፣ በ1981 ዓ.ም ከቤተሰቦቹ ጋር ወደ አሜሪካ ሄዶ ቦስተን መኖር ጀመረ፡፡ 13ኛ ዓመት በዓሉን ያከበረው እዚያ ነው፡፡ ቦስተን ማሳቹሴት ት/ቤት 9ኛ ክፍል ገብቶ፣2ኛ ደረጃን አጠናቀቀ፡፡ ከዚያም ከማሳቹሴት ዩኒቨርሲቲ  በኢኮኖሚክስ የመጀመሪያ ዲግሪውን አገኘ፡፡ ፍላጎቱ በቢዝነስ መሰማራት ስለነበረ፣በተማረው ትምህርት ተቀጥሮ አልሰራም፡፡ ከታላቅ ወንድሙ ጋር ቦስተን ውስጥ “ባሻ” የተባለ የኢትዮጵያ ሬስቶራንት ከፍተው መስራት ጀመሩ፡፡ ሀብታሙ፤አዲስ አበባ ህዝቡን የሚያሳትፍ፣የተሟላ ደህንነት ያለው፣ዘመናዊና ርካሽ የትራንስፖርት ሲስተም ያስፈልጋታል ይላል፡፡ ከተማዋ እያደገች እንደሆነ ጠቅሶ፣ አዳዲስ፣ መብራታቸው የሚሰራ፣ ፍሬናቸው ያልተበላሸ፣ ነዳጅ በየመንገዱ የማያልቅባቸው፣ ሁልጊዜ ፍተሻና ሰርቪስ የሚደረግላቸው፣ … ዘመናዊ ታክሲዎች ያስፈልጋታል ብሏል፡፡ ስለዚህ በኢንተርኔት የሚሠራ ሲስተም አዘጋጅቷል፡፡ አዲሱ ሲስተም ሞባይል ስልክ ላይ የሚጫን አፕሊኬሽን ነው፡፡ የታክሲ አገልግሎት ፈላጊው በጣቱ ሲስተሙን ሲነካ፣ ታክሲው በጥቂት ጊዜ ውስጥ ፈላጊው ያለበት ቦታ ይመጣለታል፡፡ ታክሲው ሲመጣ፣ ታርጋው፣ የአሽከርካሪው ስምና ፎቶ ለፈላጊው ይደርሳል፡፡ ለአሽከርካሪው ደግሞ የአገልግሎት ፈላጊው  ስም፣ ስልክ ቁጥርና ፎቶ ይደርሰዋል፡፡ ታክሲ ፈላጊው ስብሰባ ቦታ ወይም ገበያ መኻል ወይም ቢሮ አካባቢ ቢሆን፣ታክሲ አሽከርካሪው የአገልግሎት ፈላጊውን ማንነት በቀላሉ እንዲያውቅ ይረዳዋል፡፡ የታክሲው ሰሌዳ ቁጥርም ፈላጊው ዘንድ ስላለ በቀላሉ ሊያውቀው ይችላል፤በማለት ሀብታሙ አስረድቷል፡፡ ይህ ሲስተም ሁሉንም ሰው ተጠቃሚ ያደርጋል ይላል፡፡ በአሁኑ ወቅት ከተማው ውስጥ ባሉ አሮጌ ላዳዎች ኅብረተሰቡ ካልተቸገረ በስተቀር አይጠቀምም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ የሚጠይቁት ዋጋ በጣም ውድ ስለሆነ ነው፡፡ ለትንሽ ርቀት የሚጠይቁት 50 እና 60 ብር ነው፡፡ እኛ ግን የምናስከፍለው መንግስትና ማኅበራቱ በሚወስኑት ታሪፍ በኪ.ሜትር አስልተን ነው፡፡ በዚህ አይነት ህዝቡ በተመጣጣኝ  ዋጋ አገልግሎት ያገኛል፡፡ አሁን ያሉት ላዳ ታክሲዎች  ብዙ ጊዜ ቆመው ነው የሚውሉት፡፡ የእኛ ታክሲዎች ግን ብዙ ምልልስ ያደርጋሉ፡፡ ለምሳሌ ፒያሳ የሄደ ታክሲ ባዶውን አይመለስም፤ከሄደበት ሌላ ተጠቃሚ ይዞ ይመለሳል፡፡ አሁን የሚገቡት አዲስ ታክሲዎች 750 ናቸው፡፡ ለከተማው ህዝብ በሙሉ አገልግሎት ለመስጠት በቂ አይደሉም፡፡ ስለዚህ አሁን በአገልግሎት ላይ ያሉትንም አሮጌ ላዳዎች እንጠቀማለን፡፡ በዚህ ዓይነት ብዙ ምልልስ ሲያደርጉ ጥሩ ገቢ ያገኛሉ፤ መኪናቸውንም ይቀይራሉ፤የከተማዋንም እይታ ይለውጣሉ፡፡
በከተማዋ ካሉት 26 ማኅበራት ውስጥ ከ6ቱ ጋር ለመስራት ባለፈው እሁድ መፈራረሙን ሀብታሙ ገልጿል፡፡ አብዛኞቹ የተፈራረሙባቸው ጉዳዮች ስነ ምግባርን የተመለከተ ነው፡፡ ታክሲ እያሽከረከሩ ጫት መቃም፣ ሲራ ማጨስ፣ ቤንዚን ሳይሞሉ መጓዝና መንገድ ላይ ማቆም፣ መጠጥ ጠጥቶ  ማሽከርከር፣ … ተጠቃሚዎች ወደ ታክሲ እንዳይመጡ ስለሚያደርጉ ክልክል ናቸው፡፡ የተሳፋሪው ደህንነት እንዲጠበቅ፣ ዕቃ (ሞባይል፣ ገንዘብ፣--) ረስቶ ቢወርድ ሾፌሩ ተጠያቂ ይሆናል፡፡ በነዚህ ነጥቦች ላይ ነው ተስማምተው የተፈራረሙት፡፡ ሌላው የዛይ ራይድ ጥቅም ለተማሪዎች አገልግሎት መስጠት ነው፡፡ ሲስተሙ ላይ የተማሪዎች አፕሊኬሽን አለ፡፡ አንድ ወላጅ ልጆቹን ት/ቤት ማድረስ የማይችልበት ሁኔታ ቢፈጠር፣ ዛይ ራይድን ጠርቶ ት/ቤት እንዲያደርስለት ማድረግና ልጆቹ ት/ቤት እስኪደርሱ በስልካቸው መቆጣጠር ይችላል፡፡ ታክሲው የት ጋ እንደታጠፈ፣ ስንት ደቂቃ እንደፈጀበት፣ የት እንደደረሰ፣ ልጆቹ ከታክሲው ወርደው ት/ቤት ሲገቡ፣ በሲስተሙ ይከታተላል፡፡  
ዛይ ራይድ፤አዲሶቹ ታክሲዎች እስኪገቡ ድረስ አይጠብቅም፡፡ በሚቀጥለው ሳምንት በ130 ላዳ ታክሲዎች ሥራ እንደሚጀምር ሀብታሙ ተናግሯል፡፡ አሁን ባጃጆችን አልመዘገቡም እንጂ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ከከተማ ወጣ ወዳሉ ኮንዶሚኒየሞች የሚያደርሱ ባጃጆችን ለማሰማራት ዕቅድ አለው፡፡ ይህን ሲስተም ለመስራት 2 ሚሊዮን ዶላር (40 ሚ.ብር ገደማ) ያህል በጀት መድበው ነበር የተነሱት፡፡ ነገር ግን በየጊዜው አዳዲስ ነገሮች ስለሚጨመሩና የተሰራውም በየጊዜው መሻሻል ስላለበት፣ወጪው ከተገመተው በላይ ከፍ ማለቱን ሀብታሙ ታደሰ ተናግሯል፡፡ ይህ ሲስተም ከተጀመረ አራት ወይም አምስት ዓመት ቢሆነው ነው፤ይላል ሀብታሙ፡፡ በአሜሪካ ማሳቹሴትስ ከተማ የጀመረው UBR የተባለ ኩባንያ ነው፡፡ ይህ ኩባንያ በዓመት 60 ቢሊዮን ዶላር ያንቀሳቅሳል፡፡ ሲስተሙ በጎረቤት አገር ኬንያም እየተሰራበት ነው፡፡ ሲስተሙ ከተጀመረ ወዲህ የኬንያ አሽከርካሪዎች ገቢ በሦስት እጥፍ ማደጉን ሃብታሙ ገልጿል፡፡ ለአዲስ አበባ የላዳ ታክሲ ባለቤቶችም ሆነ ለአዲሶቹ የታክሲ ባለንብረቶችና ሹፌሮች ተስፋ ሰጪ ዜና ይመስላል፡፡ አገልግሎቱ በፍጥነት ከተስፋፋ ደግሞ የከተማዋ ነዋሪዎችንም ከታክሲ ወረፋ ግፊያ ይገላግል ይሆናል፡፡     


                   


Save for Later/ በኋላ ለማንበብ ያስቀምጡ
   
Up vote :18     Down vote :0     Ajeb vote :18

    Ajebnew Email

    Subscribe to ajebnew email for daily, weekly and/or monthly feeds and everything worth your time will be right in your inbox!


    WE ARE STORYTELLERS. BE SURE TO NEVER MISS ANYTHING.