Top

18

“የፓስታና ማካሮኒ ፋብሪካ ማቋቋም ነው እቅዴ”

Saturday 30th of July 2016 12:34:02 PM  |  Admas Trade and Economy

የበልግ ምርት ምን ይመስላል፣ የመኸር ዝግጅቱስ፣ ባለፈው ዓመት በተከሰተው ድርቅ የተጎዱ አርሶ አደሮች በምን ሁኔታ ላይ ይገኛሉ፣ የዕርዳታ አሰጣጡስ፣ ጎርፍ ያስከተለው ጉዳትስ፣ የግብአት (ምርጥ ዘር፣ ማዳበሪያ) አቅርቦትና የግብርና ባለሙያዎች ድጋፍ ምን ይመስላል? ---በሚል የመንግሥት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት፣ የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ሚ/ርና ብሔራዊ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን በጋራ ባዘጋጁት ጉዞ፣ባለፈው ሳምንት፣ በኦሮሚያና በደቡብ ክልል ዞኖች በተዘዋወርንበት ወቅት በጊኒር ወረዳ የሚገኘውን የአስቻለው ካሳዬን የእርሻ ልማት ድርጅትና የሌሎችንም ለማየትና ባለቤቶቹንም ለማነጋገር ዕድል አግኝቼ ነበር፡፡
አቶ አስቻለው ካሳዬ በባሌ ዞን ጊኒር ወረዳ፣ ጊኒር ከተማ 01 ቀበሌ ነው ተወልዶ ያደገው፡፡ በ40ዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኘው ጎልማሳው፤የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን የተማረውና የ2ኛ ደረጃ ትምህርቱን ያጠናቀቀው እዚያው ጊኒር ከተማ ነው፡፡ አቶ አስቻለው ትምህርት እንደጨረሰ ሥራ ፍለጋ ወደ ሀለባ ከተማ ሄዶ ነበር፤ በመኻሉ የማይክሮ ፋይናንስ ብድር ዕድል ተመቻቸለት፡፡ ብድሩን ወስዶ እየሰራ ሳለ የእህል ንግድ ድለላ ጀመረ፡፡ ከዚያም እህል እየገዛ ለተለያዩ ፋብሪካዎች በታማኝነት ሲልክ ቆየ። የሚያገኘውም ገንዘብ እየበረከተ መጣ፡፡ በዚህ ጊዜ፤ ‹‹ለምን የራሴን ሥራ አልሠራም?” የሚል ሐሳብ መጣለት፡፡ ስላሰበው ነገር ባለቤቱን ወ/ሮ አዳነች ከበደን አማከራትና እሷም በፕላንት ሳይንስ ዲፕሎማ ስላላት በሙያዋ እንደምታግዘው እርግጠኛ ሆና እንዲቀጥልበት አበረታታችው፡፡
በኢንቨስትመንት ለመሠማራት ቢፈልግም በየትኛው ዘርፍ እንደሚሰማራ አልወሰነም ነበር። እህል እየገዛ ለፋብሪካዎች ሲያቀርብ ቆይቷል። ሥራውን ያውቀዋል፡፡ ስለዚህም ለምን በእህል ምርት አልሰማራም? በማለት የስንዴ ምርት እርሻ ኢንቨስትመንት ፈቃድ አወጣ፡፡
የእርሻ መሬቱን በ2001 ተረክቦ፣ በቀጣዩ ዓመት በአንድ ሚሊየን ብር ያህል ካፒታል በ208.4 ሄክታር መሬት ላይ እርሻ ጀመረ፡፡ የተለያየ መጠን ያለው እህል እያመረተ ሲሸጥ ቆይቷል፡፡ በአካባቢው በዓመት ሁለቴ ነው የሚያመርቱት - በበልግና በመኸር፡፡ ከአንድ ሄክታር መሬት ላይ ከ60-65 ኩንታል ምርት ያገኛል፡፡ ዘንድሮ ከሄክታር 65 ኩንታል ለማግኘት አቅዷል - 13546 ኩንታል ማለት ነው፡፡ የእህል ዋጋ ተለዋዋጭ ነው፤ አንዴ ከፍ ሌላ ጊዜ ደግሞ ዝቅ ይላል፡፡ አንድ ኩንታል ስንዴ በአማካይ 800 ብር ይሸጣል፡፡ በዚህ ስሌት መሠረት ከዘንድሮ ምርት ከ7-8 ሚሊዮን ብር እንደሚያገኝ ገምቷል፡፡ ድርጅቱ ሌሎች ነገሮችም እንደ ጥራጥሬ፣ አብሽ፣ ነጭ ሽንኩርት… ያሉትን ያመርታል፡፡
ኢንቨስተሩ በስንዴ እርሻ ላይ ብቻ ተወስኖ መቅረት አይፈልግም፡፡ የማካሮኒና ፓስታ ግብአት የሆነው ስንዴ በእጁ ስላለ፣ በጊኒር ከተማ የማካሮኒና ፓስታ ፋብሪካ የማቋቋም ዕቅድ አለው፡፡ አቶ አስቻለው የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ ከሆነችው ከወ/ሮ አዳነች ከበደ ያፈራቸው የ4 ልጆች አባት ነው፡፡ ወ/ሮ አዳነች ሙያዋን ተጠቅማ እርሻው አስፈላጊውን ፓኬጅ እንዲጠቀም፣ በወቅት እንዲዘራና በወቅቱ እንዲታረም እንደምታደርግ ገልጻለች፡፡ የአካባቢው አርሶ አደሮች አቶ አስቻለውን እንደሚወዱት ሰምተናል፡፡ ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ ይሰጣቸዋል። በመሰመር እንዲዘሩም ይመክራቸዋል። በዚህም የተነሳ ማሳውን እንደ ራሳቸው እርሻ ነው የሚያዩት።

                   


Save for Later/ በኋላ ለማንበብ ያስቀምጡ
   
Up vote :18     Down vote :0     Ajeb vote :18

    Ajebnew Email

    Subscribe to ajebnew email for daily, weekly and/or monthly feeds and everything worth your time will be right in your inbox!


    WE ARE STORYTELLERS. BE SURE TO NEVER MISS ANYTHING.