Top

18

“ዘንድሮ ከሄክታር 90 ኩንታል እንጠብቃለን”

Monday 8th of August 2016 06:05:24 AM  |  Admas Trade and Economy

 በድርቁ የተጎዱ፣የምርጥ ዘርና የማዳበሪያ መግዣ አጥሯቸዋል
     በባሌ ዞን አጋርፋ ወረዳ ኢላጊጎዳሪ ቀበሌ ማዳበሪያ ሲገዙ ያገኘናቸው ወ/ሮ ከበቡሽ መንግሥቱ ገበሬ ናቸው፡፡ የ45 ዓመቷ ወይዘሮ፤5 ልጆቻቸውን የሚያሳድጉት አርሰው በሚያገኙት ገቢ ነው፡፡ አምና ብዙ አርሶ አደሮች በድርቁ ሲጎዱ፣ ወ/ሮ ከበቡሽ ጥሩ ምርት ማግኘታቸውን ይናገራሉ፡፡ ‹‹አምና ድርቅ አልጎዳኝም፤ ጥሩ ምርት አግኝቻለሁ፡፡ 4 ሄክታር መሬት ነው ያለኝ፤ ከአንድ ሄክታር 50 ኩንታል አግኝቻለሁ፡፡
‹‹በዚህ ዓመትም የተሻለ ጥሩ ምርት ለማግኘት ጥሩ ዝግጅት እያደረግን ነው፡፡ የእርሻ መሬቴን አራት ጊዜ አርሻለሁ፣ አንድ ጊዜ ነው የሚቀረኝ፡፡ አምና ዩሪያና ዳኘ ነበረ የተጠቀምኩት፡፡ ዛሬ የገዛሁት ዳፕ ነው፤ዩሪያ አላገኘሁም፡፡ ዳፑን 650 ብር ነው የገዛሁት፡፡ ምርጥ ዘርም ኩንታሉን በ800 ብር ገዝቻለሁ፡፡ የግብርና ባለሙያዎች ጥሩ ምርት እንድናገኝ ያሠለጥኑናል፤ በመስመር እንድንዘራ ይመክሩናል፤የመሬቱ ለምነት እንዲጨምር ዳፕና ዩሪያ ደባልቀን እንድንጠቀም፣ አረምና እንክርዳድ እንዳይወጣ ኬሚካል ያቀርቡልናል፡፡ በአጠቃላይ አብረን ነው የምንሠራው ማለት እንችላለሁ›› ብለዋል፡፡
አርሶ አደር አደም ሁሴን፤በአጋርፋ ወረዳ የአሊ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው፡፡ አቶ አደምን ያገኘነው ለመኸር እርሻ መሬታቸውን ሲያዘጋጁ ነው፡፡ አቶ አደም በግላቸው 6 ሄክታር መሬት አላቸው፡፡ በኮንትራትና በእኩል ክፍያ የወሰዱት መሬት ስላለ፣ በአጠቃላይ 15 ሄክታር እያለሙ ነው፡፡ የቀበሌው ዋነኛ ምርት ስንዴ በዓመት አንዴ ነው የሚመረተው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ በአካባቢው በቂ ዝናብ አይጥልም፡፡ ‹‹በበልግ የሚዘራው ገብስ፣ በቆሎ፣ ጤፍ፣ አተር፣… ናቸው፡፡ በአሁን ሰዓት የሚታየው የእነዚህ ሰብሎች ቡቃያ በጣም ጥሩ ነው፡፡ ባለፈው ዓመት የተከሰተው ድርቅ፤ አሊ ቀበሌ ይሻላል እንጂ ከጎናች ባሉ ቀበሌዎች አማለማ፣ ኤልምዲ፣አንድ ሌላ ቀበሌ ድርቅ ያስከተለው ጉዳት ከፍተኛ ነው፡፡ እህል ጠፋ፤ ከብቶች ተጎዱ፣ ሞቱ፡፡
 በዚህ ዓመት የዝናቡ አመጠጣጥ ጥሩ ስለሆነ፣ የእኛም ዝግጅት እንደዚያው ያማረ ነው፡፡ ማሳው አራቴ ታርሷል፣ ዘርና ማዳበሪያ ተገዝቷል፣ አንዴ አርሰን ለመዝራት ዝግጁ ነን፡፡›› ብለዋል፡፡
መንግሥት፣ የግብአት (ምርጥ ዘር፣ ማዳበሪያ…) አቅርቦት ቢያሟላም ጥቂት ችግሮች መኖራቸውን አቶ አደም አልሸሸጉም፡፡ ‹‹ማዳበሪያው ቢቀርብም አምና ስላላረስን መግዣ ገንዘብ አጥሮናል፡፡ ዘርም በግብርና ቢሮ በኩል ቢዘጋጅም እንደየፍላጎታችን አይደለም፤ ለሁሉም አልደረሰም፡፡ ነዋሪው ማዳበሪያና ምርጥ ዘር መግዣ ገንዘብ የለውም፡፡ ወረዳው እያደረገ ያለው ጥረት ቢኖርም ለሁሉም ማዳረስ አይችልም፤ በጣም አነስተኛ ነው፡፡ በድርቁ በጣም ተጎድተን ስለነበር መንግሥት ድጋፍ እንዲያደርግልን እንጠብቃለን፡፡›› በማለት አስረድተዋል፡፡ ስለ ማዳበሪያ ዋጋ መወደድ ሌሎች አርሶ አደሮችም ተናግረዋል፡፡
 አምና በአቶ አደም ማሳ አካባቢ መጠነኛ ዝናብ ጥሎ ስለነበር ብዙ አልተጎዱም፡፡ ‹‹ከሌሎች የተሻልኩ ነኝ›› ይላሉ፡፡ ዘንድሮ የአየር ሁኔታው ጥሩ ስለሆነና በዚሁ ዓይነት ከቀጠለ በሄክታር ከ80-90 ኩንታል እንደሚጠብቁ ገልጸዋል፡ ‹‹አምና ምንም ምርት አልነበረም ማለት ይቻላል፡፡ በሄክታር ከ20-30 ኩንታል ነው የተገኘው፡፡ ካቻምና (2006) ከ80-90 ኩንታል ስላገኘን ዘንድሮም እንደዚያ ነው የምንጠብቀው፡፡›› በማለት አጠቃለዋል፡፡
አቶ ጁሐር ጀማል፤ የአጋርፋ ወረዳ ግብርና ጽ/ቤት ም/ኃላፊ ነው፡፡ ወረዳው ዝናብ አጠር እንደሆነ ጠቅሶ አምና መጀመሪያ ላይ ዝናቡ ጥሩ ስለነበር፣ 12ሺህ ሄክታር መሬት መታረሱን፣ ነገር ግን ወደ ኋላ ላይ ዝናቡ ስለጠፋ ከፍተኛ ጉዳት ማስከተሉን፤ ዘንድሮም በመጋቢትና ሚያዝያ የጣለው ከፍተኛ ዝናብ ባስከተለው ጎርፍ 851  ሄክታር መሬት መጎዳቱን ገልጿል፡፡ የዘንድሮ በልግ ዝናብ አመጣጥና አጣጣል  ጥሩ ነው፡፡ በበልግ የተዘራው እህል በአንድ ማሳ እያደገ፣ በሌላው ደግሞ እየደረቀና እየታጨደ ስለሆነ፣ ከአምናው የተሻለ 300 ሺህ ኩንታል እህል ይገኛል ብሎ እንደሚገምት ተናግሯል፡፡  
አቶ ጁሐር ለመኸሩ ከፍተኛ ዝግጅት መደረጉን፣ መጪውን የአዝመራ ወቅት አስመልክቶ በጽ/ቤቱ ውይይት መደረጉን፣ ለግብርና ባለሙያዎችና ለአርሶ አደሮች ምን ማድረግ እንዳለባቸው፣እንዴት በዘመናዊ መንገድ ማረስ እንደሚገባቸው ሥልጠና መሰጠቱንና የቴክኒክ ድጋፍ መደረጉን ገልጿል፡፡ በወረዳው ካሉት 13,500 አርሶ አደሮች መካከል 93 በመቶ ለሚሆኑ ሥልጠና መሰጠቱን፣ ከታቀደው 18 ሺህ ኩንታል ማዳበሪያ ውስጥ 11 ሺህ ኩንታል በቀበሌ ማኅበራት በኩል በየቀበሌው እንዲደርስ እየተደረገ መሆኑን፣ ከኦሮሚያ ምርጥ ዘር ኢንተርፕራይዝ የተገኘ ምርጥ ዘር በወረዳው በሁለት ማዕከል ቀርቦ አርሶ አደሮች እየገዙ መሆናቸውን፤ በድርቁ ጉዳት የደረሰባቸውና በወረዳው አነስተኛ ገቢ ያላቸው 1,440 አርሶ አደሮች  ተለይተው፣ ከኦሮሚያ አነስተኛና ብድርና ቁጠባ፤ ብድር እንዲያገኙ እየተመቻቸ መሆኑን እንዲሁም ባለፈው ዓመት በድርቅ ለተጎዱ አርሶ አደሮች መንግሥት 4 ሺህ ኩንታል እህል ሰጥቶ መከፋፈሉን ተናግሯል፡፡
ም/ኃላፊው፤ በተለያዩ ምርቶች 89 ክላስተሮች ለማደራጀት አቅደው፣82 ክላስተሮች በማደራጀት ልጠና መሰጠታቸውን፤ በአራት ቀበሌዎች አርሶ አደሩ በገበያ ተፈላጊ የሆኑ ምርቶች እንደሚያመርት፣ አምና በተለያዩ ቀበሌዎች ያባዙት 7,921  ኩንታል ዘር ስላለ፣. ይህንን ዘር ከኦሮሚያ ምርጥ ዘር ኢንተርፕራይዝ ከገዙት ጋር እንዲጠቀሙ እንደሚደረግ ገልጿል፡፡ አንዳንድ አርሶ አደሮች የማዳበሪ ዋጋ ተወዷል ያሉትን አቶ ጁሐር አይቀበለውም፤ እንዲያውም ከአምናው የቀነሰ ነው ብሏል፡፡
ከዘንድሮ እርሻ 13 ሚሊዮን ኩንታል አንጠብቃለን
በዶዶላ ወረዳ ከባድ ዝናብ ጥሎ ኮረብታ ሰር ባለው በቀጨማ ጨፌና ገነታ ቀበሌዎች በ198 ሄክታር መሬት ላይ የተዘራ የስንዴ ማሳያ ያወደመው ሐምሌ 9 ቀን 2008 ዓ.ም ነው፡፡ ዝናቡ ከባድ መሆኑን፣ 2 ኪ.ሜ ከፍ ብሎ የሚገኘውን ወንዝ ድልድይ ሰብሮ ማሳዎቹን ማጥለቅለቁን በአደጋው ማግስት ከባሌ ዞን ስንመለስ በስፍራው ተገኝተን ተመልክተናል፡፡
ወ/ሮ ዲንሾ ብርቢሳ ማሳቸው በጎርፍ ከወደመባቸው አርሶ አደሮች አንዷ ናቸው፡፡ ድጋሚ ጎርፍ መጥቶ እርሻቸውን እንዳያወድም ከቤተሰቦቻቸው ጋር በማሳቸው አናት ቦይ ሲሰሩ ነው ያገኘናቸው፡፡ የወ/ሮ ዲንሾ መሬት 3 ሄክታር ተኩል ነው፡፡ 3 ኩንታል ማዳበሪያ ተጠቅመው ነበር ምርጥ ዘር ስንዴ የዘሩት፡፡ አሁን በእጃቸው ምንም ገንዘብ ያላቸውም፡፡ ወቅቱ ሳያልፍባች መልሰው ለመዝራት የመንግሥትን ድጋፍ ነው የሚጠብቁት፡፡ የ12 ልጆች እናት የሆኑት ወ/ሮ ዲንሾ በምን ያህል ገንዘብ እንዲሸጡ አያስታውሱም እንጂ ከአምናው እርሻ 190 ኩንታል እህል ነው ያገኙት፡፡ጎርፍ የተከሰተው ሌሊት ነው፡፡ ጧት ሰዎች መጥተው የሆነውን ነገሩን፡፡ ከግብርና ባለሙያዎች ጋር መጥተን ስናየው በ198 ሄክታር መሬት ላይ የተዘራው ሰንዴ ወድሟል፡፡ ያለው የዶዶላ ወረዳው ም/አስተዳዳሪና የግብርና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ፌኔት አማን ነው፡፡ እነዚህን አርሶ አደሮች ጊዜው ሳያልፍባቸው መልሰው እንዲዘሩ ወራዳው ዘርና ማዳበሪያ በነፃ ለመስጠት ወስኗል፡፡ ስለዚህ ማሳቸው የወደመባቸውን አርሶ አዳሮች እየለየን ነው ብሏል፡፡
ከዘንድሮ እርሻ 13 ሚሊዮን ኩንታል እህል እንጠብቃለን ያሉት ደግሞ የምዕራብ አርሲ አስተዳደርና የግብርና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ቶላ ገዳ ናቸው፡፡ አቶ ቶላ ስለ አምናው ድርቅ፣ ለዘንድሮው እርሻ አርሶ አደሩ እያደረገ ያለውን ዝግጅት ፤ ስለግብአት  አቆርቦት እንዲህ ሲሉ አጫውተውናል፡፡አምና በምዕራብ አርሲ ዞን ከ12 ወረዳ 7ቱ በድርቅ የተመቱ ነበር፡፡ ሁለት ወረዳዎች ደግሞ በዝናብ ብዛት ተጎድተዋል፡፡ አምናል በድርቅ የተጠቁ 126 ቀበሌዎች ሲሆኑ 307 ሺህ ሕዝብ ተጎድቷል፡፡ ሕዝቡ ከቤቱ እንዳይፈናቀል፤ ከቤቱ ርቆ እዳይሰደድ ከመንግሥትና መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጀቶች ጋር ብዙ ሥራ ሰርተረናል፡፡ ሕዝቡ በምግብ እጥረት እንዳይጎዳ በተለይ ሴቶችና ሕፃናት የምግብ አቀርቦት እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡ ዘንድሮ በድርቅ ለተጎዱት ቀበሌዎች ምርጥ ዘርና ማዳበሪ በነፃ ሰጥተናል፡፡ በአጠቃላይ በእኛ ዞን 28 ሚሊዮን ብር ተመድቦ ስንዴ፣ በቆሎ፣ ጤፍ፣ ገብስ፣… የመሳሰሉን እህሎች ገዝተን ለዘር ሰጥተናል፡፡ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅቶችም ይህን ያህል ገንዘብ አዘጋጅተው 13,600 ኩንታል ምርጥ ዘር በሁሉም ወረዳ አከፋፍለናል፡፡
በአምናው ድርቅ የሞተ ሰው የለም፡፡ በጎርፍ ግን ዘጠኝ ሰዎች ሞተዋል፡፡ 806 አባወራዎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ወደ ቤታቸው መመለስ ያልቻሉ 39 አባወራዎች አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረግን ነው፡፡ በጎርፍ የተጠቁ ወረዳዎች ሻላ፣ ሰራሮ በከፊል ሻሸመኔ በተወሰነ ደረጃ ደግሞ ዶዶላ እንዲሁም በዚህ ሳምንት የተከሰተ በገደብ አሳሳ ወረዳዎች ነው፡፡ በምርጥ ዘርና በማዳበሪያ አቅርቦ ምንም ችግር የለም ማለት ይቻላል፡፡ የማደበሪያ አቅርቦት ትንሽ ዘግይቶ ነበር፡፡ በአሁኑ ወቀት ከአቅዳችን 91 በመቶ አስገብተን 64 በመቶ ደግሞ አከፋፍለናል፡፡
በምርጥ ዘር በኩል ምንም ችግር የለም፡፡ በዞኑ 252,445 አርሶ አደር አለ፡፡ በበልግ 1.3 ሚሊዮን ኩንታል አንጠብቅ ነበር፡፡ ነገር ግን በድርቁ ምክንያት 900 ሺህ ኩንታል ነው ያገኘነው፡፡ በመኸር 13 ሚሊዮን ኩንታል እህል ለማግኘት አቅደናል፡፡ በዚህ ደግሞ በቂ ዝግጅትና ክትትል አድርገናል፡፡ ለዚህ የክረምት ወቀት 346 ሺህ ሄክታር መሬት የተዘጋጀ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 97 በመቶው ታርሷል፤ 61 በመቶው ተዘርቷል፡፡ ቀሪውን ደግሞ በቀጣይ ጊዜ እንሸፍናለን፡፡›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡

                   


Save for Later/ በኋላ ለማንበብ ያስቀምጡ
   
Up vote :18     Down vote :0     Ajeb vote :18

    Ajebnew Email

    Subscribe to ajebnew email for daily, weekly and/or monthly feeds and everything worth your time will be right in your inbox!


    WE ARE STORYTELLERS. BE SURE TO NEVER MISS ANYTHING.