Top

18

ዛሬ የከበሩ ማዕድናት ጋለሪ ይከፈታል

Monday 29th of August 2016 10:57:08 AM  |  Admas Trade and Economy

ግቢው ንፁህ ነው፡፡ ዙሪያውን የተለያዩ ቀለማት (አረንጓዴ፣ሰማያዊ፣ነጭ) ባላቸው የከበሩ ማዕድናት ተውቦ ሲያዩት ልብን በሐሴት ይሞላል፡፡ በስተግራ በኩል ግድግዳው ላይ የተለያዩ ባህላዊ አልባሳትና ቅርፃ ቅርፆች ተደርድረዋል፡፡ ጥግ ላይ የቡና ማፍያ መደብ አለ፡፡ መኻሉ ቡና መጠጫ በርጩማ ተደርድሯል፡፡ ፊት ለፊት ያሉት በመስተዋት ያሸበረቁ ሁለት ክፍሎች ከከበሩ ማዕድናት የተሠሩ ጌጣጌጦች (ጅውለሪ) የሚሸጡባቸው ናቸው፡፡ ፎቅ ላይ የአርት ጋለሪ አለ፡፡
ይህ አሁን ያስቃኘኋችሁ ግቢ፣ ዛሬ ከ11 ሰዓት ጀምሮ ተመርቆ የሚከፈት ሲሆን በተለምዶ አትላስ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ከኡራኤል ወደ ቦሌ ሲሄዱ ከ‹‹2000 ሐበሻ ሬስቶራንት›› ፊት ለፊት የሚገኘው የአብዘር ኢሳያስ ትሬዲንግ የከበሩ ማዕድናትና ጌጣጌጦች ባህላዊ አልባሳት ቅርፃ ቅርፅ… ጋለሪ ነው፡፡
የዓለምን ኦፓል ገበያ የተቆጣጠረው የአውስትራሊያ ኦፓል ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት የወሎ ኦፓል ዓለም ገበያ ውስጥ ሰብሮ መግባት ችሏል። ኦፓሉ ከማማሩም በላይ ያንፀባርቃል፡፡ የተለያዩ የኦፓል ዓይነቶች በተለያዩ የአገሪቷ ክፍሎች ይገኛሉ። በሰሜን ሸዋ የሚገኘው ኦፓል በተለምዶ ‹‹ቸኮሌት ኦፓል›› ይባላል፡፡፡ በአፋር ክልልም ተገኝቷል፡፡ የዛሬ 5 ዓመት ገደማ የወሎውን ኦፓል ሲያዩት በጣም ወደዱት፡፡ ኢትዮጵያ ያልተነካ የማዕድን ሀብት ስላላት በዚህ ዘርፍ ለመሰማራት ወሰኑ፡፡
ጥናት ለማድረግ ወደተለያዩ አገራት በመሄድ በኦፓል ኤግዚቢሽኖች ተሳተፉ፡፡ ከዚያም የውጪውን የገበያ ሥነ- ሥርዓት አዩ፡፡ በዚህ ጊዜ የበከበሩ ማዕድናት ሥራ አዋጪና በዓለም ተፈላጊ መሆኑን ተገንዝበው፣ ወደ ሥራው መግባታቸውን የአብዘር ኢሳያስ ትሬዲንግ  መሥራች ባለቤትና ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ኢሳያስ አበበ ይናገራሉ፡፡
አብዘር ኢሳያስ ትሬዲንግ ላለፉት 10 ዓመታት በኮምፒዩተር፣ የጽሕፈት መሳሪያዎች፣ በቲኬትና አስጎብኚነት፣ ወደ ኋላም በማዕድን ኤክስፖርትነት ሊሰራ የቆየ ድርጅት ነው፡፡ በአሁን ወቅት የድርጅቱ ራዕይ ኢትዮጵያ ያሏትን የከበሩ ማዕድናት ማስተዋወቅና የገጽታ ግንባታ መሆኑን አቶ ኢሳያስ ይናገራሉ፡፡
ከገጽታ ግንባታው አንዱ ቱሪስቶችን ወደ አገሪቷ መሳብ ነው፡፡ የዚህ ጋለሪ መከፈት በጣም ለሚቸኩሉ፤ አንድ ቀን ወይም ግማሽ ቀን ብቻ ለሚቆዩ ቱሪስቶች በአንድ ግቢ ውስጥ አምስት ዓይነት አገልግሎት ማግኘት በጣም ጥሩ አማራጭ ነው ይላሉ አቶ ኢሳያስ፡፡ ‹‹የሚቸኩሉ ቱሪስቶች ሽሮ ሜዳ፣ ጥቁር አንበሳ አካባቢ ወይም መርካቶ ለመዘዋወር ጊዜ አይኖራቸውም፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ቪዛ ካርዳቸውን ሊነጠቁ፤ ፓስፖርታቸውን ሊጠፋ፣… ይችላል፡፡ እኛ ጋ ግን ደህንነታቸው ተጠብቆ ባህላዊ ቡና እየጠጡና ሥዕል እየተመለከቱ አምስት ዓይነት አገልግሎት ያገኛሉ›› ብለዋል፡፡
ድርጅቱ በአንድ ግቢ ከሚሰጣቸው 5 ዓይነቶች አገልግሎቶች አንዱ የባህል ዕቃዎች (ሱቬኒር)፣ ቅርፃ ቅርፅ፣ የባህል አልበሳት፣ የስጦታ ዕቃዎች ናቸው። ሌላው አገልግሎት፣ ማዕድናትን በተለያዩ መልኩ አለስልሶና (ፖሊሽ አድርጎ) እሴት ጨምሮ መሸጥ ነው፡፡ ሦስተኛው ደግሞ የአርት (ሥዕል) ጋለሪ ነው፡፡ ‹‹ብዙ ቱሪስቶች አርት (ሥዕል) ይወዳሉ፡፡ ምስላቸው ወዲያው ተሠርቶ እንዲሰጣቸው ይፈልጋሉ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያውያን ባለሀብቶች ጥሩ ጥሩ ቤቶች እየሠሩ ነው፡፡ ቤታቸው ውስጥ የሚሰቀሉ ጥሩ ጥሩ ሥዕሎች ይፈልጋሉ፤ ይገዛሉ፡፡ ለዚህ ነው የታዋቂ አርቲስቶችን ጋለሪ ያዘጋጀነው›› በማለት ገልጸዋል፡፡
ሌላው ዝግጅት የአገራቸውን ባህል የሚያስተዋውቁበት የጀበና ቡና ሥነ-ሥርዓት ነው። በቡናው ዝግጅት ላይ ለቁርስ የሚሆን አበሻ ዳቦ፣ ጭኮ፣ ዳቦ ቆሎ፣ አምባሻ፣ ፈንዲሻ… ይቀርባል። አምስተኛው አገልግሎት አስጎብኚ ድርጅት (ቱር ኤንድ ትራቪል) ነው፡፡ በዚህ ሥራ፣ የተለያዩ የአገሪቱን ውብና ታሪካዊ ቦታዎች ያስተዋውቃሉ፤ የመኪና ኪራይም ያቀርባሉ፡፡
ጋለሪው በሚመረቅበት ዕለት የከበሩ ማዕድናት ወርክሾፕ ለሕዝብ ክፍት ሆኖ የሚታይ ሲሆን ‹‹ማዕድናቱ እንዴት ነው የሚቀረፁትና የሚለሰልሱት ጌጣጌጦች እንዴት ነው የሚሰሩት፣ የሚለውን ጥያቄ ይመልሳል፡፡ በዚሁ የመክፈቻ ዕለት የሥዕል ወርክሾፕም ይታያል፡፡ አርቲስቶች አንዴት ነው የሚሥሉት ለሚለው ጥያቄ አርቲስቶች በቀጥታ ሲሰሩ የሚታዩበት (Live) ወርክሾፕ ይቀርባል፡፡ ቱሪስቶች ቡና እየጠጡ ሥዕል ሲሳል ማየት፣ ምስላቸውን ማሠራት ወይም እንዲህ አይነት ነገር ሳልልኝ ሊሉ ይችላሉ›› በማለት አቶ ኢሳያስ አስረድተዋል፡፡
የጋለሪው መከፈት ኢትዮጵያ ያላትን 42 ዓይነት የከበሩ የተፈጥሮ ማዕድናትን ማስተዋወቅ ነው ያሉት አቶ ኢሳያስ፣ “ባለሀብቶች በዚህ ዘርፍ ኢንቨስት ቢያደርጉ ጥቅሙ ዘርፈ ብዙ ነው፡፡ ‹እናተም ትጠቀማላችሁ፣ ለአገሪቷም ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ታስገኛላችሁ፤ ለበርካታ ዜጎችም የሥራ ዕድል ትፈጥራላችሁ፡፡ ስለዚህ ባለሀብቶች ሆይ! ይህን ያልተነካ ድልብ የተፈጥሮ ሀብት ዘርፍን እንደ አንድ ምቹ አጋጣሚ (ኦፖርቹኒቲ) ተመልከቱ የሚል መልዕክትም አለው” በማለት አብራርተዋል፡፡
በማንኛውም ዘርፍ ችግሮች እንዳሉት ሁሉ በማዕድን ዘርፍም መኖሩን የጠቀሱት አቶ ኢሳያስ፣ “አሁን የከበሩ ማዕድናት ማምረቻ የለንም፤ ገበሬዎቹ አምርተው የሚሰጡንን ኤክስፖርት ስለምናደርግ የምርት እጥረት አለ፡፡ ሌላው ደግሞ አምራቾች የዓለምን ዋጋ በትክክል ስለማያውቁ፣ ሁሉንም ምርት በተገኘው ዋጋ ይተምናሉ። ስለዚህ እኛም ቦታ ተረክበን ወደ ማምረት ለመግባት እንቅስቃሴ ጀምረናል” ብለዋል፡፡
አቶ ኢሳያስ ለወደፊት ሁለት ዕቅዶች አሉኝ ይላሉ። “ኢትዮጵያ የወርቅ ማዕድን ካላቸው አገሮች አንዷ ናት። ወርቅ ኤክስፖርት ታደርጋለች፡፡ ብርና ወርቅን በከበሩ ማዕድናት ብናስጌጣቸው (ብንጨምርባቸው) ወርቅን ከምንሽጥበት ሦስትና አራት እጥፍ ዋጋ ሊያወጡ  ይችላል፡፡ የወርቁን እሴት ይጨምረዋል፡፡ የተወሰኑ የከበሩ ማዕድናት ዋጋቸው ከወርቅ በላይ ነው፡፡ ስለዚህ ኤክስፖርት ለማድረግ የጌጣ ጌጥ (የጅውለሪ) ኢንዱስትሪ (ፋብሪክ) መክፈት እፈልጋለሁ፡፡ ሌላው ደግሞ በእጅ የተሰሩ መስቀሎች ያላቸው ወርቆች ዋጋቸው ውድ ነው። ወርቆቹ ላይ የተለያዩ የከበሩ ማዕድናት በማድረግ ደረጃውን የጠበቀ ጌጣጌጥ ወደ አሜሪካ፣ አውሮፓ፣ ካናዳ፣ ኤክስፖርት ማድረግ የወደፊት ዕቅዴ ነው” ሲሉ ገልፀዋል፡፡
የአብዘር ኢሳያስ ትሬዲንግ ለ50 ዜጎች የሥራ ዕድል ፈጥሯል፡፡ ባለሀብቱ፣. የተከበሩ ማዕድናትን ይዘው በዓለም 1ኛ በሚባለው በአሜሪካ አሪዞና ግዛት ቱሳይና በዴንቨር፣ በአውሮፓ፣ በፈረንሳይ፣ በጀርመን፣ በቻይና ሆንግኮንግ፣ በቅርቡ ደግሞ በታይላንድ ኤግዚቢሽኖች በመሳተፍ የኢትዮጵያን የከበሩ ማዕድናት እያስተዋወቁ መሆኑን አቶ ኢሳያስ አበበ ተናግረዋል፡፡   

                   


Save for Later/ በኋላ ለማንበብ ያስቀምጡ
   
Up vote :18     Down vote :0     Ajeb vote :18

    Ajebnew Email

    Subscribe to ajebnew email for daily, weekly and/or monthly feeds and everything worth your time will be right in your inbox!


    WE ARE STORYTELLERS. BE SURE TO NEVER MISS ANYTHING.