Top

18

ወደ ከተማነት እየተለወጡ ያሉ የባሌ ገጠር መንደሮች

Saturday 30th of July 2016 12:23:52 PM  |  Admas Trade and Economy

በበልግ የተዘራው የስንዴና የበቆሎ ቡቃያ የተከረከመ መስሎ መሬቱን አረንጓዴ ምንጣፍ አልብሶታል፡፡ አሁን ወቅቱ ስንዴ የሚዘራበት ነው። ዞኑ በተራሮቹና በቱሪስት መስህብነቱ ቢታወቅም አብዛኛው መሬ ለጥ ያለ ነው፡፡ ዙሪያውን ቢመለከቱ፣ እዚህም እዚያም በስንዴና በበቆሎ ሰብል የተሸፈኑ አነስተኛ ማሳዎች ያገኛሉ፡፡ ለመኸር እርሻ እየተዘጋጁና እየለሰለሱ ያሉ መሬቶችም ያያሉ። የቻሉትን ያህል ርቀት በዓይንዎ ቢያማትሩም፣ የወዲያኛውን ጠርዝ ማየት የማይቻልበት፣ በሰፊ ሄክታር መሬት የታረሱ እርሻዎችም ያስተውላሉ-በባሌ ዞን፡፡
የባሌ ዞን በእርሻ ሰብል ምርቶች ይታወቃል፤ በተለይም በስንዴና ገብስ ምርቱ፡፡ ሌሎች ሰብሎችንም ያመርታል - በቆሎ፣ ማሽላ፣ ቦለቄ፣ ቀይና ነጭ ሽንኩት…፡፡ አንዳንድ ሰዎች የባሌ ዞን ሁኔታዎች ቢመቻችለትና መንገድ ቢኖረው፣ ኢትዮጵያን በምግብ ሰብል ማጥገብ ይችላል ይላሉ። ዞኑ ያለበት የመንገድ ችግር በጣም ከፍተኛ ነው። እድሳት የማያውቅ፣ የጠጠርና ጥርጊያ መንገዶች ይበዛዋል፡፡
በቅርቡ፤ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት፣ የእርሻና የተፈጥሮ ሀብት ልማት ሚ/ርና ብሔራዊ የአደጋ ስጋትና ሥራ አመራር ኮሚሽን በጋራ፣ አልኒኖ ያደረሰውን ጉዳት፣ ከጉዳቱ ያገገሙ አርሶ አደሮች የበልግ እርሻና የመኸር ዝግጅት፣ የዕርዳታና የግብአት አቅርቦት ስርጭት ምን እንደሚመስል፣ የጎርፉ አደጋ ያስከተለውን ጉዳት…እንዲመለከቱ የጋዜጠኞች ቡድን ወደ ሰሜን፣ ምሥራቅና ደቡብ ክልሎች ለሥራ ጉብኝት ልከው ነበር፡፡ ዛሬ በደቡብ ክልል በባሌ ዞን ስዘዋወር ያየሁትንና ያስገረመኝን በወፍ በረር ላስቃኛችሁ፡፡
እኛ በተዘዋወርንባቸው ወልተኢ አቶታ፣ ቀበና፣ አቃሻና አርዳቶሬ ቀበሌዎች፣ ማዕድ ቤት ካልሆኑ በስተቀር የሳር ክዳን ቤቶች አላየሁም፡፡ የገጠሩ ሕዝብ በብዛት ሞተር ሳይክል ይጠቀማል፡፡ በገጠር መንገዶች ሴቶችንም ሆነ ወንዶችን አፈናጥጦ መጓዝ የተለመደ ነው፡፡ የዚህ ምክንያቱ ምን ይሆን? በማለት የባሌ ዞን መንግሥት ኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አብዱልሐኪም አሊዩን ጠየቅሁ፡፡
አቶ አብዱልሐኪም ሲመልሱ፣ እንደሚታውቀው ባሌ ትርፍ አምራች ከሚባሉ ዞኖች አንዱ ነው። አርሶ አደሩ በጥሩ ሁኔታ ያመርታል፤ ጥሩ ምርትም ይሰበስባል፡፡ በዚህም ኑሮው እየተለወጠ ነው። እንደምታዩት በየቀበሌዎቹ፣የሳር ቤት የለም። ቤታቸው ውስጥም የተመረጡ ዕቃዎች ነው ያሉት። ጥሩ አልጋ፣ ኮንትሮል ቡፌ፣ … የመሳሰሉት፡፡ ሌላው የሚገርመው ነገር ሞተር ሳይክል በየቤቱ አለ ለማለት ያስደፍራል፡፡ በአንድ ቀበሌ ውስጥ ቢያንስ ከ100-150 ሞተር ሳይክሎች አሉ፡፡ ገበሬው ራሱ ገዝቶ ራሱ ይነዳል፡፡ ገበሬው፣ እንደ ድሮው ፈረስ መግዛት አቁሟል፤ሞተር ሳይክል ነው የሚገዛው፡፡ ለምሳሌ 300 ሰዎች ለስብሰባ ቢጠሩ፣ ከ150 በላይ የሚሆኑት ባለሞተር ሳይክል ናቸው፡፡ ቀበሌዎቹ ትርፍ አምራች ስለሆኑ፣ ብዙ ምርት ያመርታሉ፡፡ ለምርታቸው ማስቀመጫ ከቆርቆሮ ቤታቸው ጎን ትላልቅ የቆርቆሮ መጋዘን አላቸው፡፡
የአርሶ አደር የሆኑ ዘጠኝ ቀበሌዎች አሉ፡፡ እነዚህ ቀበሌዎች በዓመት በበልግና በመኸር ሁለት  ጊዜ ያመርታሉ፡፡ በዚህ ዓይነት ህዝቡ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ ጥሩ ሁኔታ ላይ ነው ያለው፡፡ በባሌ ዞን፣ ዘጠኝ የአርብቶ አደር ቀበሌዎች  አሉ፡፡ ለስሙ አርብቶ አደር ይባሉ እንጂ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ህይወታቸው እየተለወጠ ነው፡፡ ከብትም ያረባሉ፣ እርሻም ያርሳሉ፡፡ ከአርብቶ አደርነት ወደ ግብርና እየመጡ ነው፡፡ አርብቶ አደር ሲባል እንደ ድሮ ብዙ ከብቶች መንዳት ሳይሆን የተመረጡ ፍየሎችና ግመሎች እያደለበ፣ለገበያ በማቅረብ ጥሩ ገንዘብ እያገኘ ነው፡፡ እንደ አገር ማለት ይቻላል፤ በጊኒር ወረዳ ኦዳ የሚባል የከብቶች ገበያ አለ፡፡ እዚያ ነው የግመል ገበያ ያለው፡፡ ከዚያ ተገዝተው ነው ወደ ውጭ የሚጫኑት፡፡ ትልቁ ከ30 ሺህ እስከ 40 ሺህ ብር ይሸጣል፡፡
ገበሬዎቹ መኪናም አላቸው፡፡ መኪና የሌለው ቀበሌ የለም ማለት ይቻላል፡፡ የጭነትና የህዝብ ማመላለሻ መኪና በየቤቱ ጥግ ቆሞ ነው የሚታየው። በሺናና ወረዳ ውስጥ የሚገኝ ጎሞራ የሚባል ቀበሌ አለ፡፡ መረጃውን ካገኘሁት ትንሽ ቆይቻለሁ እንጂ በዚያ ቀበሌ ብቻ 22 የህዝብ ማመላለሻ ነበር፡፡ በጎሮ ወረዳ ወልተኢ ሰኢዳ ቀበሌም፣ የዚያኑ ያህል አለው፡፡ ግለሰብ አርሶ አደሮች በግል መኪና ገዝተው በማኅበር ይደራጃሉ፡፡ ይህ የሚያሳየው ገበሬው ከእርሻ ተነስቶ ወደ ኢንዱስትሪ እየተሸጋገረ መሆኑን ነው፡፡ በሀገር አቀፍ ደረጃ በሄክታር ከፍተኛ ምርት ያገኘው አርሶ አደርም ያለው እዚሁ ነው፡፡ በጊኒ ወረዳ ወልቴኢ በተባለው ቀበሌ ሙዘሚል አብደላ የተባለ አርሶ አደር፤ ከአንድ ሄክታር 113.28 ኪ.ግ ምርት አግኝቷል፡፡ ይህ ገበሬ ትራክተርም ገዝቶ፣ ለራሱም እያረሰ፣ህዝቡን እያገለገለ ነው፡፡ ይህ ገበሬ ከእርሻ ወደ ኢንዱስትሪ እየተሸጋገረ ነው፡፡   
የባሌ ዞን ዌብ፣ ገናሌ ያዶት … የተባሉ ትላልቅ ወንዞች አሉት፡፡ ከአገሪቷ የቱሪስት መስህቦች
አንዱ የሆነው ሶፍ ኦማር ዋሻም የሚኘው በባሌ ነው፡፡ ከባሌ ተራሮች ፓርክ የሚነሳው ዌብ ወንዝ፤ የዲንሾን፣ የአጋርፋን፣ የገተራን፣ የጎሮን፣ የጊኒር ወረዳዎችን አቋርጦ፣ ሶፍ ኦማር ዋሻ ይገባል፡፡ ከዚያም ዋሻውን ውስጥ ለውስጥ 7 ጊዜ አቋርጦ ሁሉቃ በሚባል ቦታ ወጥቶ፣ ወደ ሶማሊያ እንደሚፈስ፣አቶ አብዱልሐኪም አሊዩ አጫውተውኛል፡፡

                   


Save for Later/ በኋላ ለማንበብ ያስቀምጡ
   
Up vote :18     Down vote :0     Ajeb vote :18

    Ajebnew Email

    Subscribe to ajebnew email for daily, weekly and/or monthly feeds and everything worth your time will be right in your inbox!


    WE ARE STORYTELLERS. BE SURE TO NEVER MISS ANYTHING.