Top

18

በአጋርነት መስራት ውዴታ ሳይሆን ግዴታ ነው!

Saturday 9th of July 2016 10:47:38 AM  |  Admas Trade and Economy

የቴክኖሎጂ ሽግግር ማለት ማሽነሪ ማምጣት አይደለም

   የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ትራኮን ያለበትን ደረጃ ጥናት አድርጋችሁ ድክመታችንንና ማድረግ ያለብንን ብትነግሩን የፈለገውን ገንዘብ እከፍላለሁ፡፡ 400 ሚሊዮን ብር ቢሆንም ለመክፈል ዝግጁ ነኝ፡፡ ምክንያቱም አሁን ያወጣሁትን ወደፊት በእጥፍ እንደማገኘው አውቃለሁ፡፡
አቶ ተክለብርሃን አምባዬ
የተክለብርሃን አምባዬ ኮንስትራክሽን መስራችና ባለቤት በትራኮን ውስጥ እንዴት አድርገን ነው የቴክኖሎጂ ሽግግር ማድረግ የምንችለው? የቴክኖሎጂ ሽግግር ምንድነው? እኛ አሁን ምን ደረጃ ነው የምንገኘው? ዓለም የደረሰበት ደረጃ የት ነው? ክፍተታችን ምንድነው? እንዴት ነው ክፍተቱን ማጥበብ የምንችለው? … በሚሉ ርዕሰ ጉዳዮች ተክለብርሃን አምባዬ ኮንስትራክሽን (ቲኤሲ) የ2008 ዓ.ም ሲምፖዚየም ባለፈው ማክሰኞ በሂልተን ሆቴል አዘጋጅቶ ነበር፡፡
በዝግጅቱ ላይ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሲቪልና ኢንቫይሮመንታል ኢንጂነሪንግ ት/ቤት ፕሮፌሰር አበበ ድንቁ፤ “ፓርትነርሺፕ ኤንድ ጆይነት ቨንቸር ፕራክቲስ ፎር ቴክኖሎጂ ትራንስፈር ኢን ኢትዮጵያን ኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ” በሚል ርዕስ ጥናታዊ ጽሑፍ አቅርበው ነበር፡፡ አቶ ዘውዱ ተፈራም “ኮንትራት አድሚኒስትሬሽን ኤንድ ክሌም ማኔጅመንት ፕራክቲስ ፎር ቴክኖሎጂ ትራንስፈር” በሚል ርዕስ ጥናታዊ ጽሑፍ አቅርበዋል፡፡ መድረክ መሪው ደግሞ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሊጂ ፋከልቲ ፕሮፌሰር ዳንኤል ቅጣው ነበሩ፡፡
በኢትዮጵያ የቴክኖሎጂ ሽግግር እየተባለ ብዙ ጊዜ ይነገራል እንጂ እውነተኛ የቴክኖሎጂ ሽግግር እንደሌለ ይነገራል፡፡ ፕሮፌሰር ዳንኤል ቅጣው ስለ ቴክኖሎጂ ሽግግር ምንነት ሲናገሩ፣ “ለቴክኖሎጂ ሽግግር መሰረተ ልማት ያስፈልጋል፡፡ አንዱ መሰረተ ልማት የሰው ኃይል ነው፤ የእውቀት ደረጃ፡፡ ቴክኖሎጂ ያደገበት የዳበረበት፣ የለመደበት ቦታ አለ፡፡ ከዚ ቦታ ወዳልተለመደበት ስፍራ ስናመጣው፣ ቴክኖሎጂውን ተቀባይ ያስፈልጋል፡፡ ተቀብሎ ማወቅ፣ ማጥናት መልመድ ያስፈልጋል፡፡ ከዚያም ከሀገሪቱ የኢኮኖሚ ሁኔታ ጋር ያያይዘዋል፤ ያዛምደዋል፡፡ ከዚያ በኋላ ያሻሽልና አዲስ ቴክኖሎጂ ይፈጥራል፡፡ በዚህ ጊዜ ነው የቴክኖሎጂ ሽግግር ተፈጠረ የሚባለው፡፡
የቴክኖሎጂ ሽግግር ማለት ማሽነሪ ማምጣት አይደለም፡፡ ማሽነሪ አንዱ አካል ነው፡፡ ብዙ ጊዜ የምንሳሳተው ማሽነሪ፣ ኮንክሪት፣ ሚክሰር … በማምጣታችን የቴክኖሎጂ ሽግግር ያመጣን ይመስለናል፡፡ ይህ አንዱ ክፍል ነው፡፡ የቴክኖሎጂ እውቀት ከማሽነሪ አሰራር፣ ከማርኬቲንግ፣ ከዲዛይን፣ ከኮንትሮል ሲስተም፣ … ከማሽነሪ ጋር ስናደርግ ነው የቴክኖሎጂ ሽግግር የሚፈጠረው በማለት አስረድተዋል፡፡
ፕሮፌሰር አበበ ድንቁ አፅንተው የተናገሩት፣ የኮንስትራክሽን ድርጅቶች በጋራ፣ በሽርክና በትብብር ቢሰሩ ውጤታማና ተወዳዳሪ መሆን እንደሚችሉ፣ ከዚህ ውጭ አማራጭ እንደሌለ ምሳሌ በመጥቀስ አስረድተዋል፡፡ በእኛ አገር መንገዶች፣ የባቡር ሀዲድ፣ እንደ ዳንጎቱ ያሉ ትላልቅ ፋብሪካዎች … እየተሰሩ ያሉበት በቻይና ኩባንያዎች ነው፡፡ እና በእዚህ ግንባታዎች አልተሳተፍንም ያሉት ፕሮፌሰር አበበ፣ ለምን? ቢባል አቅም የለንማ! ስለዚህ በተቻለ መጠን ፓርትነርሺፕ ፈጥረን መወዳደር አለብን፡፡
እኛ አገር አሸዋ፣ ጠጠር፣ … አቅራቢ ትልቅ ድርጅት የለም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ እያንዳንዱ ደረጃ 1 ኮንትራክተር የእንጨት፣ የብረት … ወርክሾፕ አለው፡፡ በእነዚህ ሁሉ ጥራት ያለው (ፐርፌክት) አይደለም፡፡ ስለዚህ እነዚህን ነገሮች የሚሰራ ራሱን የቻለ እህት ኩባንያ ማቋቋም ያስፈልጋል፡፡ በዚህ ረገድ ትራኮን እህት ኩባንያ በማቋቋም ከተለመደው አሰራር ወጣ እያለ ነው፡፡ ለምሳሌ ኤድናሞል የመዝናኛ ኢንዱስትሪ ነው .. በ10ሩም ክፍለ ከተሞች ቅርንጫፍ ቢከፍት ተክለብርሃን አምባዬ ኮንስትራክሽን ይሰራዋል፡፡ ይህ ዓለም አቀፍ አሰራር ነው፡፡
የኮንስትራክሽን ዘርፍ ብዙ ዝርዝሮች አሉት፡፡ አንዳንድ የኮንስትራክሽን ድርጅቶች በአንድ የተወሰነ ዘርፍ ስፔሻላይዝድ መሆን አለባቸው፡፡ እንጨት ሲፈልግ ከእገሌ፣ ብረት ሲፈልግ ከእገሌ፣ ኮንክሪት ሲፈልግ ከእገሌ … መባል መቻል አለበት፡፡ ኮንትራክተሮቻችን በተወሰኑ ዘርፎች ስፔሻላይዝድ ማድረግ አለባቸው፡፡ ያለበለዚያ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ሆነን ወደ ገበያ መግባት አንችልም፡፡ ስለዚህ የተለያየ ስፔሻሊቲ ያላቸው የኮንስትራክሽን ድርጅቶች ፓርትነርሺፕ መፍጠር አለባቸው፡፡
ቀደም ሲል ከ10 ዓመት በፊት ኢትዮጵያ ገበያ ውስጥ የቻይና፣ የኮሪያ፣ የጃፓን፣ የቱርክ፣ … ኮንትራክተሮች ነበሩ፡፡ አሁን ግን ቻይና ብቻ ነው በገበያው ያለው፡፡ ምክንያቱም ስትራቴጂያቸው ሌሎችን አዳክሞ ከገበያ ማውጣት ነው፡፡ አሁን ቻይኖቹ የሚሰሩበት ዋጋ ከበፊቱ ይቀንሳል? አይቀንስም፤ በጣም ውድ ነው፡፡   
ትላልቆቹ ደረጃ አንድ ኮንትራክተሮች የራሳቸው ሳይት አላቸው፡፡ ጥሩ ነው ለገበያ ይሸጣሉ? አይሸጡም፡፡ መሆን ያለበት ለራሳቸውም ተጠቅመው ለገበያም መሸጥ አለባቸው፡፡ በአንድ ወቅት 10 ሺህ ሜትር ኩብ ጠጠር ፈልገን የሚያቀርብ ጠፋ፡፡ አሸዋ፣ ጠጠር፣ ኮንክሪት … ማቅረብ የኩባንያ ስራ ነው፡፡ ደረጃውን የጠበቀ 10 ሺህ ሜትር ኩብ 02 ደረጃ ጠጠር እፈልጋሁ ብል የሚያቀርብ ድርጅት የለም፡፡ ስለዚህ የተለያየ ስፔሻሊቲ ያላቸው ድርጅቶች ውህደት ፈጥረው አቅማቸውን ማዳበር አለባቸው፡፡ ውህደት ሲፈጠር፣ ዋጋ ይቀንሳል፣ ጥራት፣ ተወዳዳሪነት፣ ፍጥነት … ይጨምራል፤ ዓለም አቀፍ ገበያ ውስጥም ለመግባት ተወዳዳሪ መሆን ያስችላል፡፡ በዓለም አቀፍ ገበያ በኬንያ፣ ታንዛኒያ፣ ሱዳን… ተወዳዳሪ ሆነህ ስትሰራ ለአገሪቷ የውጭ ምንዛሪ ታመጣለህ፡፡
ትራኮንም ከውጭ የኮንስትራክሽን ኩባንያዎች ጋር መስራት አለበት፡፡ ከኤስያ፣ ከአውሮፓ፣ ከአሜሪካ፣ … የኮንስትራክሽን ኩባንያዎች ፓርትነርሺፕ መፍጠር አለበት፡፡ የግድ ቀድሞ መዘጋጀት አለበት፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ህብረት ባንክ፣ ንብ ባንክ …. የዋና መ/ቤት ህንፃ እየሰሩ ነው፡፡
ማነው የሚሰራው? የቻይና ኩባንያዎች፡፡ የአገር በቀል ኩባንዎች የሉም፡፡ አቅማቸውን አዳብረው መወዳደርና መሳተፍ መቻል አለባቸው፡፡
የኮንስትራክሽን ዘርፍ ማደግ ያለበትን ያህል አላደገም፡፡ በአፄ ምኒልክ ዘመን አልፍግሬድ ኢልግ የተባለ መሃንዲስ የተጠቀመበት የእንጨት ርብራብ (ስካፎልድ) ሲስተም ነው በአሁኑ 21ኛው ክፍለ ዘመን ያሉ አገራችን የኮንስትራክሽን ኩባንያዎች የሚጠቀሙበት፤ ተመሳሳይ ነው፤ ምንም አልተሻሻለም፡፡ትርፉን ለማብዛት ለማሳደግ፣ ራስን አሻሽሎ ተስማሚ ከሆነ ድርጅት ጋር ፓርቲነርሺፕ መፍጠር ውዴታ ብቻ ሳይሆን ግዴታም ነው፡፡
 የቴክኖሎጂ ሽግግር ለማምጣት የግሉ ዘርፍ ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር መቀናጀት አለበት በማለት፤ ፕሮፌሰር አበበ ድንቁ አስረድተዋል፡፡

                   


Save for Later/ በኋላ ለማንበብ ያስቀምጡ
   
Up vote :18     Down vote :0     Ajeb vote :18

    Ajebnew Email

    Subscribe to ajebnew email for daily, weekly and/or monthly feeds and everything worth your time will be right in your inbox!


    WE ARE STORYTELLERS. BE SURE TO NEVER MISS ANYTHING.