Top

18

በሆላንዳዊ ባለሀብቶች የተቋቋመው የአበባ እርሻ

Monday 25th of July 2016 09:42:17 AM  |  Admas Trade and Economy

    ከአዲስ አበባ በ163 ኪ.ሜ ርቀት ላይ በምትገኘው የዝዋይ ከተማ ዳርቻ ላይ በተመሰረተው ሰፊ የአበባ እርሻ ልማት መንደር ውስጥ ከከተሙት አበባ አምራች ድርጅቶች በአንዱ ውስጥ ነኝ። በሆላንዳውያን ባለሀብቶች ተመስርቶ ከ1200 በላይ ለሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ቋሚ የስራ ዕድል የፈጠረው ይኸው የአበባ እርሻ ልማት AQ Rose ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር በሚል መጠሪያ ይታወቃል እ.ኤ.አ በ2006 ዓ.ም የተመሰረተው ይህ ድርጅት ሰሞኑን 10ኛ ዓመቱን በታላቅ ድምቀት ሲያከብር ተገኝቼ የእርሻ  ልማቱን ለመጎብኘትና ሆላንዳውያን ባለሀብቶቹንና የድርጅቱን ሰራተኞች ለማነጋገር ዕድሉን አግኝቼ ነበር፡፡
በየዓመቱ ከ100 ሚሊዮን በላይ አበቦችን ለአውሮፓ፣ ለጃፓንና ለዱባይ ገበያዎች እያቀረበ የሚገኘው ድርጅቱ ከፍተኛ የውጪ ምንዛሬ ገቢ በማስገኘት ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስቴር አቶ መለስ ዜናዊ የሜዳሊያና የሰርተፍኬት ሽልማቶችን አግኝቷል፡፡
የድርጅቱ ባለቤትና ዋና ሥራ አስኪያጅ ሆላንዳዊው በለሀብት ሚስተር ፍራንክ አምርላን ከዓመታት በፊት ወደ ኢትዮጵያ የመጡት የማስተርስ ዲግሪያቸውን የማሟያ የጥናት ፅሁፍ በአበባ እርሻ ልማት ላይ ለመስራት ነበር፡፡ የአበባ እርሻ ለቤተሰቦቻቸው የዓመታት የሥራ ዘርፍ ሆኖ የቆየ በመሆኑ ሚስተር ፍራንክ ዕድገታቸው ከአበባ እርሻ ጋር ነበር፡፡ ለዚህም ነበር የጥናት ፅሁፋቸው በአበባ እርሻ ላይ እንዲሆን የፈለጉት፡፡ ሥራቸውን አጠናቀው ወደ አገራቸው ሲመለሱም ነገሮችን አመቻችተው ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት በአበባ እርሻ ልማት ሥራ ላይ ለመሰማራት ወስነው ነበር። ሃሳባቸው ቤተሰባዊ ድጋፍ አግኝቶ ከታናሽ ወንድማቸው ጋር AQ Rose ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበርን አቋቁመው በ18 ሄክታር መሬት ላይ የአበባ እርሻቸውን ጀመሩ፡፡ በዘመናዊ ትምህርት የታገዘው አበባ እርሻ ስራቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ሄዶ ጥራት ያለው አበባ ምርቶችን ለአውሮፓ፣ ለጃፓንና ለዱባይ ገበያዎች በግንባር ቀደምትነት ለማቅረብ እንዲችሉ አድርጓቸዋል፡፡ በ18 ሄክታር ላይ የተጀመረው የእርሻ ስራቸውም ዛሬ ከእጥፍ በላይ አድጎ 38 ሄክታር መሬት እንዲሆን አስችሏቸዋል፡፡ በዚህ አበባ እርሻ ማሳም ከ15 በላይ የሚሆኑ የአበባ ዝርያዎችን እያመረቱ ጥራታቸውን የጠበቁ አበባ ምርቶችን ለውጪ ገበያ በማቅረብ ከፍተኛ የውጪ ምንዛሩን በማስገኘት ላይ ናቸው፡፡
ባለሀብቱ ሚስተር ፍራንክ በኢትዮጵያ ውስጥ በአበባ እርሻ ላይ መሰማራት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚያስገኝ ይናገራሉ፡፡ የአገሪቱ አየር ፀባይ አመቺነት፣ ለምርት ገበያ ምቹነቱና በቂ የሰው ኃይል ለማግኘት የሚቻል መሆኑ ከጠቀሜታዎቹ መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ዘመናዊ ትምሀርትና አዳዲስ ቴክኖሎጆዎችም ለዘርፉ እያበረከቱ ያሉት አስተዋፅኦ ከፍተኛ እንደሆነ ሚስተር ፍራንክ ይናገራሉ፡፡ “ዘመኑ በቢሮ ውስጥ ተቀምጦ በእያንዳንዱ የአበባ እርሻ ማሳ ላይ ያሉ የአበባ ምርቶች ምን ያህል ውሃና ማዳበሪያ እንደሚያስፈልጋቸው፣ ምን ያዕል ዕድገት እየሳዩ እንደሆነና በመካከላቸው በበሽታ የተጠቃ ካለ ለመለየት የሚቻልበት ቴክኖሎጂ ያለበት ዘመን ነው። ይህ ደግሞ ስራውን የበለጠ ቀላልና ምርቱ ጥራቱን የጠበቀ እንዲሆን ያስችለዋል፤” ሲሉ ይናገራሉ፡፡
የድርጅቱ የሰው ኃይል አስተዳደር ስራ አስኪያጅ አቶ አይችሉህም አበበ በበኩላቸው ድርጅቱ ስራ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ለሰራተኞች ደህንነትና ለአካባቢ ጥበቃ ከፍተና ትኩረት ሰጥቶ የሚንቀሳቀስ ድርጀት እንደሆነ ጠቁመው ለአካባቢው ማህበረሰብ አስፈላጊ የሆኑ የልማት ስራዎችን በመስራት የማህበራዊ ኃላፊነቱንም በአግባቡ እየተወጣ ያለ ድርጅት ነው ብለዋል፡፡ የድርጅቱ ሰራተኛ ልጆች ትምህርታቸውን ለመከታተል እንዲችሉ ማድረግ ድርጅቱ ከሚያከናውናቸው ተግባራት መካከል አንዱ መሆኑንና ሰራተኛው ከስራው ቢለቅ እንኳን ልጁ ከትምህርቱ እንዲፈናቀል የማያደርግ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ በቀጣዩ ዓመትም 30 የሚሆኑ የጎዳና ተዳዳሪ ልጆችን በማደራጀትና በቂ ስልጠናና ማቴሪያል በማሟላት በጫማ መጥረግ ስራ ላይ እንዲሰማሩ ለማድረግ ዝግጅቱ መጠናቀቁንም ገልፀዋል፡፡
“የአበባ እርሻዎች በአብዛኛው ኬሚካል ምርቶችን በመጠቀም ይታወቃሉ ያሉት አቶ አይችሉህም ድርጅቱ IPM (Integrated paste management) የተቀናጀ የተባይ ማጥፊያ ሥርዓትን እና 100 ፐርሰንት ነፍሳቶችን በነፍሳት የማጥፋት ቴክኖሎጂን እያተጠቀሙ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ ኬሚካል ለመጠቀም የሚያስገድዱ ጉዳዮች አንዳንድ ጊዜ በሚገጥማቸው ወቅት የአደገኝነት መጠናቸው እጅግ አነስተኛ የሆነና ወደ አገር ውስጥ በህጋዊ መንገድ እንዲገቡ የተደረጉትን ብቻ እንደሚጠቀሙም ተናግረዋል፡፡
የድርጅቱ የእርሻ ሥራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ መሃመድ አያሌው እንደሚናገሩት ድርጅቱ ጤና እና አካባቢን ሊጎዱ የማይችሉና የጎንዮሽ ጉዳታቸው እጅግ አነስተኛ የሆኑ ማዳበሪያዎችን እንደሚጠቀም ገልፀው በሽታ አምጪ ነፍሳቶችን በልተው የሚጨርሱና በሰው ጤና ላይ አንዳችም ጉዳት የማያደርሱ ነፍሳቶችን በከፍተኛ ወጪ ከውጪ አገር በማስመጣት የሚጠቀሙ መሆኑን ተናግረዋል። ይህም ነፍሳቶችን በነፍሳት የመከላከል ተግባር ለአካባቢ ጥበቃም ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳለው ገልፀዋል ይህ አሰራር በተለያዩ ጎጂ ኬሚካሎች ሳቢያ በሠራተኞች ላይ ሊደርስ የሚችለውን የጤና ጉዳት ሙሉ በሙሉ ያስቀረ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ መሆኑንም አቶ መሃመድ ተናግረዋል፡፡
የAQ Rose የአበባ እርሻ ልማት የሠራተኛ ማህበር ሊቀመንበር የሆኑት አቶ ሐያቶ ኡሺ በበኩላቸው ድርጅቱ ለሠራተኞች የሥራ ደህንነት ትኩረት እንደሚያደርግ ጠቁመው የሠራተኛውን መብት ለማስከበርም በየሁለት ዓመቱ ድርድር በማድረግ በህብረት ስምምነቱ ላይ የሠራተኛውን ጥቅም የሚያስጠብቁ ማሻሻያዎችን እንደሚያደርግ ገልፀዋል፡፡ ለሴቶች የወሊድ ፈቃድ በህጉ ከተገለፀው የአንድ ወር  ጭማሪ በማድረግ ለአራት ወራት የወሊድ ፍቃድ እንዲያገኙ አድርጓል፡፡ ‹‹ማህበሩ በድርጅቱና በሠራተኞች መካከል ድልድይ ሆኖ ድርጅቱ ትርፋማ የሚሆንበትን ሠራተኛውም የድካሙን ዋጋ በአግባቡ የሚያገኝበትን መንገድ እንዲያመቻች ያደርጋል ብለዋል፡፡ ከድርጅቱ ሠራተኞች መካክል ረዘም ላለ ጊዜ በድርጅቱ ውስጥ የሰሩ እና ከዘጠኝ ዓመት እስከ 5 ወራት የሥራ ቆይታ ያላቸው ሠራተኞች እንደሚናገሩት ድርጅቱ በአካባቢው መመስረቱ የሥራ ዕድል እንዲያገኙ እንዳደረጋቸውና በአካባቢው ካሉ ሌሎች የአበባ እርሻ ልማቶች የተሻለ የደምወዝ ክፍያና የህክምና ድጋፍ እያገኙ መሆናቸውን ይገልፃሉ፡፡ የተሻለ የሥራ አፈፃፀም ያላቸው ሠራተኞችም የተሻለ የማበረታቻና የቦነስ ክፍያዎችን የሚያገኙ መሆናቸውን ይናገራሉ። ከዚህ ሁሉ በላይ ደግሞ በአበባ እርሻ ልማት ውስጥ በስፋት ሥራ ላይ የሚውሉ ጎጂ ኬሚካሎች አለመኖራቸው ሥራቸውን ያለሥጋት ለመሥራት እንዲችሉ ያደርጋቸው መሆኑን ገልፀዋል፡፡  

                   


Save for Later/ በኋላ ለማንበብ ያስቀምጡ
   
Up vote :18     Down vote :0     Ajeb vote :18

    Ajebnew Email

    Subscribe to ajebnew email for daily, weekly and/or monthly feeds and everything worth your time will be right in your inbox!


    WE ARE STORYTELLERS. BE SURE TO NEVER MISS ANYTHING.