Top

15

በ“መስከረም ሁለት” ትዝ የሚለኝ

Monday 12th of September 2016 06:51:00 AM  |  Adebabay

(Sep 12, 2011)፡- እንዲህ እንደ አሁኑ ዓመታት አልፈው፣ አገር ቤቱም እንደ ጨረቃ ርቆ፣ ትዝታም የሕልም ያህል ቀጥኖ፣ ልቡና ዛሬን ሳይሆን ትናንትን፣ የዛሬን አዋቂነት ሳይሆን የትናንትን ልጅነት ሲናፍቅ … መስከረም ሁለትም ከአዲስ ዘመን ተርታ በትዝታ መስኮት መምጣቱ አይቀርም። የኔ ትውልድ፣ የልጅነታችን ወራት ያለፈው፣ ከመስከረም አንድ ይልቅ መስከረም ሁለት “ርዕሰ ዐውደ ዓመት” ሆኖ ነው። እንቁጣጣሽ ከዘመን መለወጫነቱ ይልቅ የመስከረም ሁለት ዋዜማ መሆኑ የታወቀ እስኪመስል ድረስ በልጅነት አዕምሯችን የተሳለው ዐቢዩ በዓል የቅ/ዮሐንስ ማግስት ነበር ማለት ይቻላል።

በዚያን ዘመን፣ የ“ግብታዊው አብዮት” በዓል የሚከበርበት መስከረም ሁለት ከመጀመሩ ወራት አስቀድሞ ዝግጅቱ እንኳን ለአዋቂዎቹ ለእኛም ለልጆቹ ይተርፈን ነበር። ክረምቱ ትምህርት ቤቶች ተዘግተው ሕጻን ወጣቱ፣ በተለይም የከተማ ልጆች፣ “ሥራ የሚፈቱበት” ወቅት ስለሆነ ቀበሌዎቹ ወጣቱን በአኢወማ፣ ሕጻናቱን በሕጻናት፣ ሴቶቹን በአኢሴማ፣ ገበሬውን በገበሬዎች ማህበር ጠምደው ዝግጅቱ ይጀመራል። ከሁሉም ዝግጅት ትዝ የሚለኝ “ሰልፍ እርገጥ” የሚባልበት ወታደራዊ ሥልጠና የመሰለ ዝግጅት ነው። ከዚህ የሚያመልጥ ማንም የለም። እናቶቻችን ራሳቸው በየዓመቱ ሰልፍ ሲማሩ፣ ከዚያም መሠረተ ትምህርት ሲማሩ፣ ትዝ ይለኛል። በመሠረተ ትምህርቱ ፊደል ለይተውበታል፣ የሰልፍ ሥልጠናው ግን አረማመዳቸውን የለወጠው አይመስለኝም።
ይኼ ሰልፍ-ሥልጠና እኛንም ሕጻናቱን አያልፈንም። ብዙ ጊዜ ከቤት ወጥተን ለመራገጡ ዕድል ስለሚሰጠን ብዙም አንጠላውም። ችግሩ የሚመጣው ሰልፍ ሥልጠናውን እንዳንቀር ከቡሄ ጭፈራ፣ ከእንጨት ሰበራ፣ ከኳስ ጨዋታ ሊከለክሉን ሲሞክሩ ነው። በተለይ አንድ ዓመት ላይ  ጅራፍ እያጮህን፣ ሆያ ሆዬ መጨፈራችንን እንድንተው የደብረ ታቦር ዋዜማ፣ ቡሄ በምንጨፍርበት ቀን፣ እስከ ማታ ድረስ ሕጻናቱን ቀበሌ አጉረው አስመሽተውናል። ዋናው የቡሄ ሰዓታችን ሲያልፍ ሁላችንንም ወደቤታችን ለቀቁን። መቸም ያዘንነው ሀዘን አይነገር። በተረፈችው ሰዓት ጓደኞቻችንን መንደር ለመንደር ፈልገን የዓመት ጥማታችንን ለመወጣት ሞከርን።


ያን ጊዜ ቡሄ የምንጨፍረው ፀሐይ ከጠለቀችበት ሰዓት እስከ እኩለ ሌሊት፣ ከዚያም በበነጋው ጠዋት ተነስተን ደግሞ ፀሐይ እስክትወጣ ድረስ ነበር። ሲነጋ ማታ የተሸለምነውን ሙልሙል እና ሳንቲም ቁጭ ብለን እንከፋፈልና ዳቦ እያመረጥን ስንገምጥ እንውላለን። ሳንቲሙ እስከዚህ ባይሆንም ከረሜላ ለመግዛት እና ሌላ ጊዜ ብዙም የማናገኘውን ለስላሳ ለመጠጣት ያስችለናል። ኋላ ኋላ ሰዉ ሙልሙል ከመስጠት ይልቅ የሳንቲም ድቃቂ መለገሱ ላይ እየበረታ ሲመጣ እኛም የምንገዛው ነገር ዓይነት ጨመር ማለት ጀምሮ ነበር። ቀበሌዎቹ ከዚህች ዓመታዊ ፌሽታን ሲያስተጓጉሉን ንዴታችን ወሰን ያጣል።


ከዚያ ግማሹን ሕጻን በኪነት፣ ግማሹን ሕጻን በሰልፍ ያሰማሩታል። ኪነት የሚገቡት ልክ እንደ ትልልቆቹ የአብዮት መዝሙሮችን አጥንተው በዕለቱ በአብዮት አደባባይ ጢም ብሎ ለሚሰበሰበው ሕዝብ እንዲዘምሩ ለማድረግ ነው። ሌሎቻችን ደግሞ እግረኛ ሰልፉን ሰልጥነን በተካነ ሁኔታ “በክቡር ትሪቡኑ” ፊት ለፊት እናልፋለን። ግማሾቻችን በባዶ እግራችን፣ ግማሾች በሸራችን፣ ግማሾች በበረባሷችን መሬቱን በትንሽ እግራችን እየደለቅን፣ እንደ ወታደርም እያደረገን።


መስከረም ሁለት ስልችት የሚለኝ የንግግሩ ብዛት ነበር። ወደቤት እንዳንሄድ እንኳን የአብዮት አደባባዩ በር ግጥም ተደርጎ ተዘግቶ መግባት እንጂ መውጣት የለበትም። ወደቤትስ ብንሄድ ማንን እናገኛለን? ቤተሰቡ በሙሉ እዚያው አደባባዩ ነው ያለው። እንጀራ ከሌማት ቆርሶ የሚሰጥ ሰው እንኳን ቤት ሳይቀር ሁሉም እንዲሄድ ግዴታ ነው። የቀረ ወዮለት። ደግሞ ልክ እንደ ቅዳሴ ሌሊት 11 ሰዓት (5ኤ.ኤም) የወጣን ቤታችን የምንመለሰው እኩለ ቀን ካለፈ በኋላ ነው። የልጅነት ሆዳችን በረሃብ ተጨራምቶ፣ በውሃ ጥም አፋችን ደርቆ። ቤት የሚቀሩት የታመሙ ወይም አረጋውያን ብቻ ይመስሉኛል።


ፕሮግራሙ ሲጀመር መድረክ መሪዎቹ በሚያንባርቅ ድምጻቸው የዕለቱን መርሐ ግብር ይዘረዝራሉ። አብዛኛው መቼም ንግግር ነው። የወጣቶች ተወካይ (አኢወማ)፣ የአኢሴማ (አብዮታዊት ኢትዮጵያ ሴቶች ማህበር ማለት ነው አዲሱ ትውልድ) ተወካይ፣ የአኢገማ (ገ=ገበሬዎች)፣ የአኢሰማ (ሰ=ሰራተኞች) ተወካይ፣ ከዚያ የዕለቱ ዋነኛ እንግዳ ንግግር ያደርጋሉ። ፍሬ ሐሳቡ አብዮታችን ከድል ወደ ድል መሸጋገሩን ማብሰር፣ ለወደፊቱም ከፊቱ የሚመጣውን ፈተና ሁሉ እየበጣጠሰ እንደሚያልፍ መተንበይ፣ የአብዮቱ ጠላቶች የሚባሉትን ከአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም ጀምሮ “መርገም” እና በመጨረሻም “ከቆራጡ መሪያችን ጋር ወደፊት” ማለት ነው። ይኸው ንግግር ነው በተለያዩ ሰዎች አንደበት ተመልሶ ተመልሶ የሚነገረው። ንግግር የማያደርገው ምንም “አኢ” የሌለን (“አኢሕማ = አብዮታዊት ኢትዮጵያ ሕጻናት ማህበር” ያልተባልነው) የእኛ የሕጻናት ተወካይ ብቻ ነው።  


በንግግሮች እና በፕሮግራሞች መካከል መርሐ ግበር አስተናባሪው “እስቲ ጓዶች፣ አንድ ጊዜ አብራችሁኝ መፈክር እንድትሉ እጠይቃለኹ” ይልና ለደቂቃዎች ያህል የመፈክር ዓይነት ያዥጎደጉዳል። ከሁሉም ትዝ የሚለኝ “ከሁሉም በላይ አብዮቱ!!” የምትለው ናት። ታዲያ እያንዳንዱ መፈክር ቢያንስ ሦስት ጊዜ ይባላል። አንዳንዱ ደግሞ መልሱ ለየት ያለ ነው። ለምሳሌ መፈክር አስባዩ (አስፈካሪው ልበለው?) “እናሸንፋለን” ሲል እኛ ተቀባዮቹ “አንጠራጠርም!!” ብለን መመለስ አለብን። አንዳንዱ ደግሞ የመፈክሩን የመጨረሻ ቃል መድገም ሊሆን ይችላል። “ኢምፔሪያሊዝም ይውደም” ሲል እኛ ደግሞ “ይውደም!!” እንላለን ማለት ነው። መፈክሩ የድጋፍ ከሆነ ግራ እጅ ወደላይ ሲነሣ፣ የተቃውሞ እና የእርግማን ከሆነ ደግሞ ያንኑ ግራ እጅ ወደታች ማድረግ ይገባል።


አንድ ቀልድ ትዝ አለኝ። እኚህ በየቀልዱ ልክ እንደ አለቃ ገብረ ሃና ስማቸው የሚነሣው የጎጃሙ ጓድ ኮምጬ ግራ እጃቸውን ሳይሆን ቀኝ እጃቸውን ሲያነሡ ያየ ሰው ጠጋ ብሎ “ጓድ ኮምጫምባው ይውደም ሲባል በግራ እጅ እንጂ በቀኝ እጅ አይደለም” ቢላቸው “ዞር በል በደንብ የሚያደቀውን እጅ እኔ መቼ አጣኹት” አሉ ይባላል። ታዲያ እኛም የሚያደቀውን ሳይሆን የማያደቀውን እያነሣን “ይውደም፣ ይውደም” ስንል አንድ-አስራ አምስት ደቂቃ ይሞላል። እኛ ሕጻናቱ “ይውደሙ” የሚባሉትም፣ “ወደፊት” የሚባሉትም ሳይገቡን ሌላው እጁን ሲያነሣ ስናነሳ፣ ሲያወርድ ስናወርድ እንቆያለን። አሁን አሁን ሳስበው ግን እኛ ልጆቹ ብቻ ሳንሆን ብዙውም ትልልቅ ሰው እንደእኛው ሳይሆን አልቀረም። አቤት የመፈክሩ ብዛት። ያኔ እንዳሰማናቸው መፈክሮች ብዛት እርግማናችን አሜሪካንን ጠራርጎ ወይ አትላንቲክ ወይ ፓሲፊክ ውቅያኖስ ሳይጨምራት መቅረቱ።


በሌላው ፕሮግራም የየቀበሌው ሰልፈኛ እና ኪነት ሲያጠና የከረመውን ያቀርባል። ሁለት ወር ላላነሰ ጊዜ አገር  ሥራ ፈትቶ እንደ ሰሜን ኮሪያና ቻይና ወይንም ሶቪየት ሕብረት የደመቀ ሰልፍ ለማሳየት መከራውን ሲበላ የከረመበትን ዝግጅት አሳይቶ ወደየቦታው ይመለሳል።  


በዚያን ዘመኑ የኪነት ሙዚቃ መድረክ ላይ ወጥተው እስካሁንም እንጀራቸው ሆኖ የዘለቀ አርቲስቶች አሉ። ስለ ዕድገት በሕብረት፣ ስለ መሠረተ ትምህርት፣ ስለ ዳር ድንበር፣ ስለ አገር አንድነት፣ ስለ ዕድገት … መቸም ያልተገጠመ ግጥም፣ ያልተሞከረ ድምጽ፣ ያልተፈተሸ ትከሻ የለም - ያኔ። ያን ጊዜ የተጀመረ ሰልፍ እስካሁን ይኸው አለ። ሰበብ ፈልጎ መሰለፍ ነው። ቀበሌ ሥራው ሰው ማሰለፍ ሳይመስለው አይቀርም።


ሰዓቱ እየገፋ ሲመጣ ሰዉም መዳከም፣ ሕጻናቱም መራብ፣ በዚያ ሽንት ቤት እንኳን በሌለበት ሁኔታ የውስጥም የውጪም ጥሪ ሲመጣ ሕዝቡ መቁነጥነጥ ይጀምራል። መቼ በሩ ተከፍቶላት እንደሚወጣ ይናፍቃል። ችግሩ በሩ ላይ የሚቆሙት አብዮት ጠባቂዎች “አይቻልም” እንጂ ሌላ ቃል የሚያውቁ አይመስሉም። ሰው ቢታመምም፣ ባይታመምም፣ ሕጻንም ቢሆን አረጋዊም ቢሆን ለሁሉም መልሳቸው “አይቻልም፣ተመለስ” ብቻ ነው። ክፋቱ እኩለ ቀን ካለፈ ዝናብ አይጠፋውም። “ክቡር ትሪቩን” ላይ ለሚቀመጡት ሳይሆን በእግሩ ሰዓታት ተጉዞ ለሚመጣውና ለሚሄደው ጭንቅ ነው። ከገጠር የሚመጣው ሰልፈኛ ወንዝ ይሞላበታል፣ ይጨልምበታል፣ የክረምት ጉዞ አስቸጋሪ ነው። ደግሞ የክረምት ጭቃ።


በዚያ ወጥቶልኝ ነው መሰለኝ “ሰልፍ” የሚባል በቴሌቪዥን ሳይ፣ መፈክር የተሸከሙ ሰዎች “እንትንን ደግፈው፣ እንትንን አውግዘው” ሲባል ትዝ የሚለኝ የያኔው መስከረም ሁለት ነው። ዛሬም “ደግፈውታል” የተባለው ነገር እኔ ራሴም የምደግፈው ነገር ቢሆንም እንኳን ያ ሁሉ ሰው ደግፎት ወጣ ለማለት ይቸግረኛል። በሆነ ነገር ሳያስፈራሩት መቼም ሁሉም ሰው “እንደ አንድ ልብ መካሪ” ሆኖ ሰልፈኛ የሚሆንበት ነገር አይገባኝም። ወይም ለእኛ አገር ብቻ የተሰጠ ልዩ የቀበሌ ሥጦታ እንደሆነ እንጃ። መስከረም ሁለት ሲመጣ ይኼ ትዝ ይለኛል።


                   


Save for Later/ በኋላ ለማንበብ ያስቀምጡ
   
Up vote :15     Down vote :0     Ajeb vote :15

    Ajebnew Email

    Subscribe to ajebnew email for daily, weekly and/or monthly feeds and everything worth your time will be right in your inbox!


    WE ARE STORYTELLERS. BE SURE TO NEVER MISS ANYTHING.